
ባሕር ዳር :መጋቢት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተያዘው ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል 19 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አጎበር ለተለያዩ ክልሎች መሰራጨቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ አስተባባሪ አቶ መስፍን ወሰን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተለያዩ ጊዜያት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚከሰቱ ወረርሽኞች መካከል ወባ አንዱ ነው። በዚህም በተያዘው ዓመት የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችል 19 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን አጎበር በተለያዩ ክልሎች ተሰራጭቷል።
እንደ አቶ መስፍን ገለጻ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከባለፈው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች የወባ ወረርሽኝ የታማሚዎች ቁጥር ጭማሪ አሳይቷል። ከፍተኛ ጭማሪ ከታየባቸው ክልሎች ውስጥም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ላይ በተለይም ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተያይዞ ጭማሪ አሳይቷል። በዚህም ተመጣጣኝ ምላሽ በመስጠት ረገድ በትኩረት በመሠራት ላይ ነው።
ከባለፉት አምስት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ከአፋር እና ሐረሪ ውጪ ባሉት ክልሎች ጭማሪ ማሳየቱን የጠቀሱት አስተባባሪው ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች በትኩረት በመሠራት ላይ ነው ብለዋል።
በተለይም በተያዘው ዓመት ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል 19 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የወባ በሽታን መቆጣጠሪያ አጎበር ስርጭት ተካሂዷል። በዚህም ለኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ እና ሶማሌን ጨምሮ በቂ የሆነ የጸረ ወባ መድኃኒቶችን ለሁሉም ክልሎች መሰራጨቱን ገልጸው፣ ወረርሽኙ ስጋት በሆነባቸው አካባቢዎች በማኅበረሰብ ንቅናቄ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በመሠራት ላይ ነው ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር፤ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና ባሉት ጤና መዋቅሮች ጋር በመሆን የወባ ታማሚዎችን ማከም፣ ለወረርሽኙ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉትን የታቆረ ውሃ ማፍሰስ፣ የአጎበር ሥርጭት፣ የቤት ለቤት የመድኃኒት ስርጭት፣ የቅኝት እና የኅብረተሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ የታማሚዎች ቁጥር፣ እንዲሁም የወረርሽኝ መጠን ከፍተኛ ለውጥ በማሳየት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል የአጎበር እጥረት አለማጋጠሙን የገለጹት አስተባባሪው በቀጣይ ክልሎች በሚያቀርቡት እና በኅብረተሰቡ ጥያቄ መሠረት ዳሰሳ ተካሂዶ አስፈላጊው የአጎበር ስርጭት የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
