
ወልድያ :መጋቢት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢማጅን ዋን ደይ ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በ19 ሚሊዮን ብር ወጭ ያስገነባቸውን የመማሪያ ክፍሎ አጠናቆ አስረክቧል፡፡
ኢማጅን ዋን ደይ ከዩኒሴፍ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው ሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ መለይ እና በራያ ቆቦ ሮቢት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነው ግንባታውን ያከናወነው ፡፡
በየትምህርት ቤቶቹ ሁለት ሁለት ብሎኮች የተገነቡ ሲኾን ስምንት የመማሪያ ክፍሎች አሏቸው፡፡
የመማሪያ ክፍሎቹ የመማሪያ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸዋል፡፡
ሌሎች የመጸዳጃ እና የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የግንባታው አካል ናቸው ፡፡ በአማራ ክልል የዩኒሴፍ ፊልድ ኦፊስ ኃላፊ ወይዘሮ ምዕራፍ አበበ ዩኒሴፍ በአማራ ክልል ከ3 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ትምህርት ቤቶች ላይ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል ፡፡
ጦርነቱ በትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ መኾኑን የገለጹት ወይዘሮ ምዕራፍ ድርጅቱ በቀጣይ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ችግሩን ለማቃለል እንደሚሰራ ተናግረዋል ፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳደሪ አቶ ጋሻው አስማሜ የትምህርት ተቋማትን ማገዝ ትውልድን መገንባት መኾኑን ገልጸው ግንባታውን ላከናወኑት ምስጋና አቅርበዋል ፡፡ በዞኑ በርካታ ከደረጃ በታች ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ጋሻው ጦርነቱ የነበረውን ችግር አባብሶታል ብለዋል ፡፡ መንግሥታዊም ኾኑ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ለትምህርት ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
ዘጋቢ:- ባለ ዓለምየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!