የለውጥ አመራር ሰጭነት ስልጠና በባሕር ዳር እየተሰጠ ነው፡፡

377

የለውጥ አመራር ሰጭነት ስልጠና በባሕር ዳር እየተሰጠ ነው፡፡

ለክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ራሳቸውን አውቀው ለሌሎች መንገድ እንዲያሳዩ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ለአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የአሻጋሪ አመራር ሰጭነት (ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ) ስልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው፡፡

የስልጠናው ዓላማ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቅማቸውን ፈትሸው ስለተቋማዊ ዕድገት እና ተግባቦት ክህሎት ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ልማትን፣ ሠላምን እና አብሮነትን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የተሻለ ለማድረግ በሚመሩት ሕዝብና ሠራተኞች መካከል መነቃቃት እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

በሀገሪቱ ከዘመናት በፊት የነበረው አንድነት እና መተሳሰብ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ በስልጠና የመሪዎችን የአዕምሮ ውቅር ማስተካከል ተገቢ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ተናግረዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስተባባሪነት የሚሰጠውን ስልጠና ‹ጴጥሮስ ኔትወርክ› የሚባል በየአሜሪካን ድርጅት እና ‘ፎርድ ቴይለር ግሩፕ’ አማካኝነት የሚሰጥ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተቀነቀነ ያለውን አሻጋሪ አመራር ሰጭነት (ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ) ጸሐፊ እና መሥራች ፎርድ ቴይለር ስልጠናውን ይሰጣሉ፡፡

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስ ለአብመድ እንደገለጹት ስልጠናው በመሪዎች ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ይሞላል ተብሎ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም የነበሩትን እሴት አልባ ልማዳዊ አሠራሮች እና የአለቃና ምንዝር ግንኙነቶችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ትብብር መቀየር እንዲሁም ሥራዎች በዕውቀት ላይ ተመስርተው እንዲተገበሩም ያስችላል፡፡

ከባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ አሠራር በተጨማሪ በቴክኒክ የታገዘ የግጭት አፈታት፣ የይቅርታ አሰጣጥ እና በፍቅር ተባብሮ የመሥራት አቅምንም ያጎለብታል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ የአሻጋሪ አመራር ሰጭነት ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላም ዘመኑ የሚፈልገውን ፍሬያማ አመራር መስጠት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

ይህንን ስልጠና የአማራ ክልል ቢሮ ኃላፊዎች እና ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች ከወሰዱት በኋላ በየደረጃው ለሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሰጥም ተገልጧል፡፡

የጴጥሮስ ኔትወርክ ተወካይ ሚስ ሊንዳ ንዋ በበኩላቸው ድርጅታቸው “የአፍሪካ መሪዎች የሰለጠኑ እና አሻጋሪ (ትራንስፎረማሽናል) መሆን እንዳለባቸው ያምናል” ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጡ የሚችሉትም በዚህ መልኩ የተቃኙ መሪዎች ሲሆኑ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ስልጠናው ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራ ክልል የሚኖረው ጥቅም የጎላ ነው›› ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር በጤና ዘርፍ፣ በምግብ እና ንጹህ መጠጥ ውኃ፣ በግብርና፣ ሴቶችን በማብቃት እንዲሁም በጎልማሶች ትምህርት እና በተለያዩ መስኮች ላይ እየሠራ መሆኑንም ነው ተወካይዋ የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous articleበዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች የበርበሬ በሽታን መከላከል በመቻሉ የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡
Next articleአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ላይ የአንበጣውን የሕይወት ዑደት ማቋረጥ ካልተቻለ ስርጭቱ አሁን ካለበትም እንደሚጭምር የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡