25 በመቶ የድንች ዱቄትን ከ75 በመቶ የስንዴ ዱቄት ጋር በመቀላቀል በንጥረ ምግብ ይዘቱ የተሻለ ዳቦ ማምረት እንደሚቻል ተገለጸ።

77
ባሕር ዳር:መጋቢት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በዋናነት በወጥነትና በቅቅል መልኩ ለምግብነት የሚውለውን የድንች ሰብል ወደ ዱቄትነትም በመቀየር ለዳቦነት ለማዋል የሚያስችል ዓውደ ጥናት ባለድርሻ እና አጋር አካላት በተገኙበት በደብረ ታቦር ከተማ ተካሂዷል፡፡
በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና ድህረ- ምርት አያያዝ ምርምር ክፍል የድንች ዱቄትን በከፊል ከስንዴ ዱቄት ጋር በመቀላቀል ለዳቦነት ለማዋል የሚያስችል የጥናት ውጤት በማውጣት የምርምር ውጤቱ ጥቅም ላይ እንዲውል አሰራሩን የማስተዋወቅ ሥራ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየሰራ ይገኛል፡፡
በደብረ ታቦር ከተማ በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ የተገኙት በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ አሰፋ የደቡብ ጎንደር ደጋማ አካባቢዎች ለድንች ሰብል ተስማሚ በመሆናቸው ምርምር ኢንስቲትዩቱ ምርታማና ከበሽታ ነጻ የሆኑ የድንች ዝርያዎችን እያስተዋወቀና ጥራት ያለው ዘር እያባዛ እያቀረበ መሆኑን ገልጸው ድንችን ከወጥነትና ከቅቅልነት በዘለለ ለዳቦነት ለማዋል የሚያችል ጥናት በኢንስቲትዩቱ በኩል ተሰርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል በተግባር የተደገፈ ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የምግብ ሳይንስና ድህረ ምርት አያያዝ ተመራማሪ አቶ አየነው መረሳ በበኩላቸው 25 በመቶ የድንች ዱቄትን ከ75 በመቶ የስንዴ ዱቄት ጋር በመቀላቀል በንጥረ ምግብ ይዘቱ የተሻለ እና ጥራቱን የጠበቀ ዳቦ ማምረት እንደሚቻል በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ድንች በትንሽ መሬት ላይ ብዙ ምርት የሚሰጥ፣ ድርቅን የሚቋቋምና በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሰብል በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው ሰብሉን በማቀነባበር ወደ ዱቄትነት በመቀየር ለዳቦነት ማዋል ከሥነ ምግብ ጠቀሜታው ባለፈ በሰብል ስብሰባ፣ ማጓጓዝና ማከማቸት ወቅት የሚከሰተውን ከ30 እስከ 50 በመቶ የምርት ብክነት በመከላከል ምርቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ያግዛል ብለዋል፡፡
ድንችን በከፊል ስንዴን እንዲተካ ማድረግ የስንዴ እጥረትን ለመቀነስ፣ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን ለመቆጠብ፣ ሥነ አመጋገብን ለማሻሻል፣ ድንች የማምረት ተነሳሽነትን ለመጨመር፣ የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያግዝም አቶ አየነው ተናግረዋል፡፡
ድንችን በዳቦነት የመጠቀም አሰራር በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ለአርሶ አደሩ፣ ዳቦ በማምረት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ለሚገኙ አካላትና ለዘርፉ ባለሙያዎች በተግባር የተደገፈ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተሰጠ እንደሚገኝም ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎችም የቀረበው የምርምር ውጤት እጅግ አበረታችና ሊስፋፋ የሚገባው ተግባር መሆኑን ገልጸው ከአዋጭነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡ ድንችን በዱቄት መልክ መጠቀም ጥራት ያለው ዳቦ ለማምረት ከማገዙም በላይ ምርምር ኢንስቲትዩቱ ባካሄደው የአዋጭነት ጥናት ወደ ዱቄትነት ቀይሮ መጠቀም አዋጭ መሆኑ መረጋገጡ በዘርፉ ተመራማሪዎች በኩል የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ ተጨማሪ የአዋጭነት ጥናቶች ይሰራሉ ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሥነ-ምግብ ማሻሻል ክፍል አስተባባሪ አቶ አብርሃም ሙሌ በበኩላቸው አሰራሩ እንዲሰፋ እና በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲለመድ አርሶ አደሩ በቤቱ እንዲሞክረውና በአነስተኛ ዳቦ አምራቾች በኩል ማስተዋወቅ እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሥራው የበለጠ እንዲሰፋ ቢሮው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡
ዘገባው፦ የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ህዝብ ግንኙነት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበደብረ ማርቆስ ከተማ በ260 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
Next articleበሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው በመለይ እና በራያ ቆቦ ሮቢት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ19 ሚሊዮን ብር ወጭ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ተጠናቀቁ ።