
ደብረ ማርቆስ :መጋቢት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በበጀት ዓመቱ ከ269 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የከተማዋን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታውቋል፡፡
አሚኮ ካነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አሳቤ ይታየውና አቶ አብርሃም ከፋለ በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለረጅም ጊዜ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡ በከተማዋ ካለፉት ዓመታት የተሻለ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡
የተጀመሩ የመንገድ ከፈታ߹የጠጠርና የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ፣ የተፋሰስና ሌሎች መሰረተ ልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜና ክረምት ከመግባቱ በፊት እንዲጠናቀቁና የከተማዋ የረጅም ጊዜ የውኃ እጥረት ጥያቄ እንዲፈታላቸውም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፡
ፈታኝ የነበሩ የወሰን ማስከበር ሥራዎች ተጠናቀው የታቀዱ የመንገድ ከፈታ፣ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ንጣፍና አንድ ኪሎ ሜትር የተፋሰስ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የመንቆረር ክፍለ ከተማ የከተማና መሰረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዘውዲቱ ጌትነት ናቸው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 269 ሚሊዮን ብር በመመደብ ኀብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተለይተው ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል። የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሥራ አሥኪያጅ መንግሥቱ ጅጋር
በከተማዋ የተጀመሩ ከአራት ኪሎ ሜትር በላይ የጌጠኛ መንገድ ንጣፍ፣ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ የተፋሰስና ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ ንጣፍ ሥራዎችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል ፡፡
የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍም ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተግባዊ እየተደረገ ነው ብለዋል ሥራ አስኪያጁ፡፡
በከተማዋ ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የመንገድ መብራት ዝርጋታ እየተከናወነ ሲኾን የደብረ ማርቆስ ከተማ ስታዲየምን ጨምሮ የንጉስ ተክለ ሀይማኖት አደባባይ አካል የኾነው ቤተ መንግሥትና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ከከተማ አሥተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከ 40 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ኅብረተሰቡ በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዘጋቢ:- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!