
የአንበጣ መንጋው ከዚህ በፊት ተከስቶ ከነበረባቸው ስድስት ወረዳዎች ስርጭቱን በማስፋት ዘጠኝ ወረዳዎችን ማዳረሱን ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ እንደገለጹት ባለፉት ሳምንታት በክልሉ የአንበጣ መንጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በባሕላዊ መንገድ፣ በሰው ኃይል እና በማሽን በመታገዝ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል፡፡
ይሁን እንጅ ከትናንት ጀምሮ በባቲ እና ኮምቦልቻ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአንበጣ መንጋ ከ45 ደቂቃ በላይ ያለማቋረጥ መስመር ሰርቶ ይበር እንደነበር ዶክተር ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡ የአንበጣ መንጋው ክልሉ ከአፋር ጋር በሚዋሰንባቸው በሰሜን ወሎ ራያ ቆቦ፣ ጉባ ላፍቶ እና ሀብሩ፣ በደቡብ ወሎ ወረባቡ፣ ቃሉ እና አርጎባ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳድር ደግሞ ባቲ፣ ደዌ ሀረዋ እና አርጡማ ፉርሲ ወረዳዎች መከሰቱን ነው ዶክተር ሰሎሞን የተናገሩት፡፡
ክልሉ የአንበጣው መነሻ ከሆነው አፋር ክልል ጋር ረጅም ኪሎ ሜትሮች የሚዋሰን በመሆኑ ተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ወደ አካባቢው እየገባ እንደሆነ ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የተናገሩት፡፡ ዶክተር ሰሎሞን እንደገለጹት ወረባቡ፣ አርጎባ፣ ባቲ እና ደዌ ሀረዋ አካባቢዎች ችግሩ የጎላ ነው፡፡ አካባቢውም ተራራማ በመሆኑ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ለመከላከል አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አውሮፕላኑም ለረጅም ዓመት አገልግሎት የሰጠ በመሆኑ በብልሽት ምክንያት በሚፈለገው ጊዜ እየሠራ አይደለም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም በተሸከርካሪ እና በሰው ኃይል መከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ወሎ ዩኒቨርሲቲም የኬሚካል፣ አልባሳት እና የመርጫ መሳሪያ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የኮምቦልቻ የእጽዋት ክሊኒክ እና ሌሎች ተቋማትን የማስተባበር ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
የአውሮፕላን ቁጥር በመጨመር ርጭቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ እና አፋር እና ሶማሌ ክልሎች ላይ እርጭቱ በተጠናከረ መንገድ በአጭር ጊዜ መካሄድ እንዳለበት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር መወያየታቸውንም ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የሜትዮሮሎጅ መረጃን ጠቅሰው ዶክተር ሰሎሞን እንደተናገሩት በቀጣይ ሰፋ ያለ ጊዜ የሚወስድ ሙቀት እና ዝናብ ስለሚኖር አየሩ ለበርሃ አንበጣው መራባት ምቹ በመሆኑ ወደ ክልሉ አንበጣው በስፋት ሊገባ እንደሚችል እና በቀጣይ የበልግ እና የመስኖ ሥራው ላይም ከፍተኛ መሰናክል ሊሆን ይችላል፡፡ ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም ለመደበኛ ሥራ የተመደበውን በጀት እንደሚያዛባ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
‹‹የአንበጣ መንጋውን በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው ችግሩ በተከሰተበት አካባቢ በሰው ኃይል፣ በተሽከርካሪ እና በአውሮፕላን ኬሚካል በመርጨት ሳይሆን አፋር እና ሶማሌ ክልል የአንበጣውን የሕይወት ዑደት ማቋረጥ ሲቻል ነው›› ብለዋል ዶክተር ሰሎሞን፡፡
የአንበጣ መንጋው ከዚህ በፊት በስድስት ወረዳዎች ተከስቶ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ዓድማሱን በማስፋት ዘጠኝ ወረዳዎችን ማዳረስ ችሏል፡፡ ይህም በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ሥራ ባለመሠራቱ የስርጭት ዓድማሱን እያሰፋ እንደሚገኝ ነው ምክትል ኃላፊው የገለጹት፡፡ አንበጣው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነፋስ ኃይል ረጅም ርቀት የመጓዝ ችሎታ ያለው በመሆኑ ሽፋኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ የጉዳት መጠኑ በቀጣይ ይፋ የሚደረግ ቢሆንም አንበጣ መንጋው በሰብል እና በመኖ ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ዶክተር ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ