በጾም ወቅት የተራበን በማብላት ፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ የፈጣሪን ትዕዛዝ መፈጸም እንደሚገባ የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ።

74
ባሕር ዳር:መጋቢት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሁለቱም በጾም ላይ ናቸው። ይህ የጾም ወቅት በሁለቱም ሐይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተወደደ እና በናፍቆት የሚጠበቅ ነው። የሁለቱም እምነት ተከታዮች በሚጾሙበት ወቅት የተራበን በማብላት የተጠማውን በማጠጣት ሊኾን እንደሚገባ የእምነቱ አባቶች ተናግረዋል።
ሊቀ ሕሩያን በላይ መኮንን ጾም ማለት ራስን ለእግዚአብሔር ማስገዛት፣ ዓለማዊ ሕይወትን ለመንፈሳዊ ሕይወት ማስገዛት ማለት ነው ብለዋል።
እግዚአብሔርን ማገልገል ህሊና እና ሰውነትን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ማለት ነው። በዚህ ወቅት ችግረኞችን እና ጦም አዳሪዎችን በማሰብ እና በማገዝ በመረዳዳት መኾን እንዳለበት ተናግረዋል።
የሚበሉት የሌላቸውን እና ጦም አዳሪዎችን መርዳትና መደገፍ ከጾም ትሩፋት አንዱ እንደኾነም ሊቀ ትጉኃን አንስተዋል።
ጾምን የምንጾም ለጽድቅ በመኾኑ ጽድቅ ደግሞ በሥራ ይገኛል። ከሥራዎች ደግሞ ድኾችን እና ጦም አዳሪዎችን የተቸገሩትን ማገዝ እና መደገፍ ነው ብለዋል። እንደ ክልላችን ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ ተፈናቃዮች ከቤት ንብረታቸው ወጥተው ሜዳ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ከእንግልትና ከረሀብ ወጥተው በልተው እንዲያድሩ የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል፣ ሐይማኖታችንም ያዝዛል ብለዋል።
የሰው ማንነቱ የሚለካው በችግር ወቅት ነው። በችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማገዝ ተገቢም አስፈላጊም ነው ብለዋል ሊቀሕሩያን በላይ መኮንን። በበጎ ሥራ ያልተደገፈ ጾም ጾም አይባልም። ጾመህ በገደፍክ ጊዜ ድኾችን አስብ እንጅ ዘመዶችህን እና የምታውቃቸውን ጎረቤቶችህን አትጥራ ተብሏል፣ ይህን የፈጣሪያችንን ትዕዛዝ በማክበር የመንግሥቱ ወራሾች ልንኾን ይገባል ብለዋል።ይኽን መሠረት በማድረግ ያለው ለሌለው በመሥጠት በማገዝ በመደገፍ መረዳዳት መተሳሰብ ተገቢ ነው በረከትም ያስገኛል ብለዋል።
May be an image of 1 person and standing
የእስልምና እምነት ተከታዩ ሸክ ከድር ያሲን አደም በበኩላቸው ረመዳን የተከበረው የጾም ወቅት ነው ብለዋል። በጾሙ የእምነቱ ተከታዮች የአምላካቸውን ትዕዛዝ እንዲያከብሩ ተጽፏል።ከተጻፈው አንዱ ማንኛውም ሰው በጾም ወቅት ካለው ሀብት 2 ነጥብ 5 በመቶውን ለድኾች እና ጦም አዳሪዎች እንዲሠጥ ታዟል።
ይኽ የፈጣሪ ትዕዛዝ መከበር አለበት። ያለው ለሌለው ሊሠጥ ግድ ነው ብለዋል። ሌላው መተዛዘን መረዳዳት መደጋገፍ በጾም ወቅት እንዲፈጸሙ የታዘዙ ነገሮች ናቸው ብለዋል። ሸክ ከድር አምላካችን ጾሙን “ጥሩ ሥራ እየሠራችሁ እንድትጾሙት ነው ያዘዝኳችሁ” ብሎናል። የአላህን ትዕዛዝ ማክበር ለክብር ያበቃል ብለዋል። በተለይ ከቤታቸው ወጥተው በሰው ሀገር ለሚንከራተቱ በረሀብ አለንጋ ለሚገረፉ ወገኖቻችንን ማገዝ መደገፍ በቁርዓናችን ተጽፏል ብለዋል። ያለው ብቻ ሳይኾን የሌላችኹም ብትኾኑ ስትጾሙ የረሀብን ልክ ካወቃችሁ ከእናንተ በላይ አጥተው ለሚራቡት ለምን አትሠጡም ተብሎ ተጽፏል ነው ያሉት።
እናም በከፋ ረሀብ እና በችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች ልትሠጡ ይገባል ብለዋል። መጾም ማለት እህል ሳይበሉ ውኃ ሳይቀምሱ መዋል ብቻ አይደለም ካለው አካፍሎ መሥጠት፣ እዝነት ማድርግ፣ መደገፍ ነው ብለዋል።
በርካታ ሰዎች በችግር ባሉበት ሀገር በልቶ ጠግቦ ከአቅም በላይ ኾኖ በደል ማድረስ አይገባም። ያለው በገንዘቡ የሌለው በጸሎት ሊያግዝ ይገባል ወንድሞቻችን በችግር ውስጥ ናቸው ብሎ ማዘን ተገቢ ነው ብለዋል።
እኔን ከሞላልኝ እኔን ከደላኝ ለሌላው ምን አገባኝ ማለት አይገባም እምነታችንም አይፈቅድም ይልቅስ በአምላካችን የታዘዝነውን በእምነት በመፈጸም ተስፋ ማግኘት አለብን ብለዋል ሸህ ከድር ያሲን።
ዘጋቢ፦ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ለመከላከያ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሳካት የትምህርት ማዕከላት ሚና ከፍተኛ ነው” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
Next articleበቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር አትሌት መዲና ኢሳ አሸናፊ ሆነች።