“ለመከላከያ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሳካት የትምህርት ማዕከላት ሚና ከፍተኛ ነው” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

71
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ የትምህርት ተቋማት ሁሉም ዜጋ ገብቶ የሚማርባቸው መደረጋቸው ለሀገር የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለፁ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃና በቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች በምህንድስናና በጤና ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 314 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃው ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈው ፤ ለመከላከያ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሳካት የትምህርት ማዕከላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመከላከያ የትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲም የተቋሙን የተማረ የኀይል ፍላጎት ከማሟላት በተጨማሪ የወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በማሻሻል ተቋሙን ሊያግዝ እንደሚገባ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ አሳስበዋል።
የሀገራችን ወጣቶችም የኢትዮጵያ መከላከያን ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ አንጋፋ አመራሮችን እና ባለሙያዎችን ባፈሩት የተቋሙ የትምህርት ማዕከላት በመቀላቀል ራሳቸውን እና ሀገራቸውን መጥቀም እንዲችሉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ባቀረቡት ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ወታደር ባለሙያዎችን ከማፍራት በተጨማሪ ከአፍሪካ ተመራጭ የትምህርትና የምርምር ማዕከል ለማድረግ የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት የተቋሙን ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችሉ የትምህርትና የምርምር ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው በስሩ የሚገኙትን ሶስት ኮሌጆችና የምርምር ማዕከሉን አቅም ለማሳደግ ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም የዩኒቨርሲቲው ኮማንዳንት ተናግረዋል፡፡
በምረቃው ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን ጨምሮ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ፤ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
በትምህርታቸው ብልጫ ላገኙ ተመራቂዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት መበርከቱን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚፈጠሩ የሰላም ችግሮችን ለማረም እንደሚሠሩም በአማራ ክልል የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች አስታወቁ።
Next articleበጾም ወቅት የተራበን በማብላት ፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ የፈጣሪን ትዕዛዝ መፈጸም እንደሚገባ የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ።