
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሠላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ሠላም እና ጸጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር “የሃይማኖት አስተምህሮ ለሠላም” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡
ስለሀገራዊ እና ክልላዊ ሠላም በሚመክረው በዚህ ውይይት እንደ ሀገር እየገጠሙ ያሉትን የሠላም ሳንካዎች በማንሳት አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦች እየተሰነዘሩበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአማራ ክልል የሃይማኖት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ መልዐከ ሠላም ኤፍሬም ሙሉዓለም “ኢትዮጵያዊያን ሰላም ናፍቆናል፤ ሁላችንም ስለሠላም መሥራት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
በሀገር ደረጃ እየተስተዋሉ ካሉ የሠላም መደፍረስ ችግሮች መካከል ሃይማኖትን ምክንያት አድርገው የሚፈጠሩ ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋሉ ነው ያሉት መልዐከ ሠላም ኤፍሬም፤ “ሃይማኖት ለኢትዮጵያዊያን ስስ ብልት መሆኑን በመገንዘብ በእኩልነት ማስተናገድ ይገባል” ብለዋል፡፡ በውይይቱም የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚወስዱትን የቤት ሥራ ለይተው መውሰድ እና የሃይማኖት አባቶችም ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የትኛውም ሃይማኖት ከሠላም ውጭ ያሉ የግጭት አማራጮችን ለልዩነት መፍቻ አድርጎ አይሰብክም ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሼህ ጁሐር ሙሃመድ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ የሃይማኖቱ ተገዥ ከሆነ በመካከሉ ግጭት እና ሠላም ማጣት አይኖርም ያሉት ሼህ ጁሐር ሙሐመድ የሃይማኖት መሪዎች ሥራችን የየሃይማኖቱን ተከታዮች ለአስተምህሮዎቻቸው እንዲገዙ ማድረግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

እንኳን ምድራዊ ችግሮች ሰማያዊ መንግሥት እንኳን የሚወረሰው በሠላም ነው ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ከሠላም በተጻራሪ የቆሙ አማራጮችን መጠቀም ተገቢ አይደለም ነው ያሉት፡፡ በተለይም ሃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚፈጠሩ ቁርሾዎችን ለማረም እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊ እና ክልላዊ ሠላምን ለማስፈን የሃይማት ተቋማት ሚናቸው የላቀ ነው ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል ሠላም እና ጸጥታ ቢሮ የሃይማኖት እና እምነት ተቋማት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አለኽኝ መለሰ ናቸው፡፡ እንደሀገርም እንደ ክልልም ከሚስተዋሉ የሠላም መደፍረስ ችግሮች መካከል ሃይማኖትን ሽፋን የሚያደርጉ ግጭቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ መጥተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ ችግሮቹ የሀገር እና ሕዝብ መሠረታዊ የደኅንነት ችግሮች ሳይሆኑ ማረም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
በውይይቱ በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ የሚስተዋሉ የሠላም ችግሮች ተነስተው ምክክር ተደርጎባቸዋል ያሉት አቶ አለኽኝ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን ወስደው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ የሰላሙ ባለቤት ሕዝቡ ራሱ ነው፤ የሠላም እንከን የሆኑ ችግሮችን በየደረጃው እያወጡ በመነጋገር የመፍትሄው አካል በመሆን ሕዝቡ ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በመልዕክታቸው፡፡
ለአንድ ቀን በሚዘልቀው የምክክር መድረክ ከሠላም ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች፣ ምሁራን፣ ከተለያዩ የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
