“አረጋውያን አባቶች ሀገራቸውን ጠብቀው ሲያቆዩ የተጠቀሙበትን ጥበብ ለትውልድ ሊያስተላልፉ ይገባል” የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር

115
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “በሰላም ማስፈን እና ግጭት ማስወገድ ላይ የአረጋውያን ሚና” በሚል መልዕክት አረጋውያን ከወጣቶች ጋር መክረዋል።
በምክክሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር ተወካይ ሰብሳቢ አቶ ህሩይ ደመላሽ፤ አረጋውያን ሀገራቸውን ለትውልድ ጠብቀው ሲያቆዩ በርካታ ዘዴዎችን መጠቀማቸውን አስታውሰዋል።
ሀገር በውጭ ወራሪ ስትወረር እና ሌሎች ችግሮች ሲገጥሟት ችግሩን ለመፍታት ተመካክረዋል። ምክራቸውንም ተግባራዊ አድርገዋል በዚህም ጠላትን ድል ነስተው ወደመጣበት መልሰዋል ብለዋል። በወቅቱ የተጠቀሙበትን ብልሀት ለወጣቶች ማስተላለፍ አለባቸውም ነው ያሉት። ወጣቶች የአረጋውያንን ምክር እና ተግሳጽ በመጠቀም የተረከቧትን ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ሊያስተላልፉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች እና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው “እኛ የአባቶቻችን ልጆች ልንኾን ይገባል” ብለዋል። አባቶቻችን ችግሮች ሲከሰቱ በዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጠው ይመክሩ ይዘክሩ ነበር ያሉት ኀላፊዋ፤ ጥፋተኛው የአባቶቹን ምክር ተቀብሎ ከተጣላው ታርቆ የበደለውን ክሶ ይኖር እንደነበር ነው ያስገነዘቡት። አሁን አሁን ወጣቶች ከአባቶቻቸው ምክር እና ተግሳጽ ይልቅ የአጥፊዎችን መንገድ መከተል በመጀመራቸው በየአካባቢው ችግቶች እየተከሠቱ ስለመሆኑ አስረድተዋል። በዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ሠዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለችግር ተዳርገዋል ነው ያሉት።
አረጋውያን ጠብቀው ያቆዩትን ባሕላቸውን ፣ወጋቸውን መተሳሰባቸውን እና መረዳዳታቸውን ለወጣቶች በማስተላለፍ ወጣቶች ለሀገር ግንባታ እንዲጠቀሙበት የማድረግ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
ወጣቶች ግጭትን እንዴት ይፈቱ እንደነበርና ችግር ሲገጥማቸው ችግሩን እንዴት እንዳለፉት ሊጠይቁ እና ሊገነዘቡ ይገባልም ብለዋል። አሁን አሁን አየተባባሰ የመጣውን የሰላም እጦት ለመፍታት ወጣቶች ከአባቶቻቸው ጋር መወያየት አለባቸው ነው ያሉት።
በምክክሩ ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ድንበር ሳይገድበን በሁሉም የሀገራችን ክፍል መኖር እንድንችል የአባቶቻችን እገዛ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በምክክሩ የኢትዮጵያ አረጋውያን እና ጡረተኞች ፌዴሬሽን ተወካዮች፣ የአማራ ክልል አረጋውያን ፣ አካል ጉዳተኞች፣ ወጣቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የሀገረ መንግሥቱን ኅልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ የሰላም ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት እየተስተዋሉ መጥተዋል” የሠላም ሚኒስትር አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ
Next articleወልድያ ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።