
ገንዳውኃ፡ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ቀጣና ከኾኑ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው።
ዞኑ ገበያ ተኮር ምርት አምራች እንደመኾኑ የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ የጭነት መኪኖች እና የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚበዙበት ቀጣና ነው።
አካባቢው ባለው የልማት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተሽከርካሪ የሚበዛበት ቢኾንም በቂ የነዳጅ ማደያ ባለመኖሩ በተለይም ደግሞ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችና በተሳፋሪዎች ላይ ችግር ፈጥሯል።
በምዕራብ አርማጭኾ ወረዳ አብርሃጅራ ከተማ የመለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪው መለሰ ወርቁ እንደገለጹልን፤ በወረዳው የነዳጅ ማደያ ባለመኖሩ ከግለሰቦች በከፍተኛ ዋጋ ነዳጅ ለመግዛት ተገዷል። ማደያ ላይ ነዳጅ ለማግኘት ደግሞ ከ150 በላይ ኪሎ ሜትር መጓዝ ግድ ኾኗል። ታዲያ የሚያወጡትን ወጭ ለማካካስ ከተሳፋሪዎች ላይ ዋጋ እንደሚጨምሩ ነው የገለጹልን።
ከአብርሃጅራ – ጋብላ 78 ኪሎ ሜትር ከሚከፈለው ታሪፍ እጥፍ እንደሚከፍሉ የነገሩን ደግሞ ያነጋገርናቸው ተሳፋሪ ጋሻው ማንነገረው ናቸው። ለዚህም ደግሞ በነዳጅ ማደያ አለመኖር ምክንያት በሚፈጠር የነዳጅ ችግር ከተሳፋሪዎች ላይ እንደሚጨምሩ አሽከርካሪዎች እንደ ምክንያት እንደሚያነሱ አንስተዋል።
የምዕራብ አርማጭኾ ወረዳ መንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ትራንስፖር ስምሪት፣ ክትትልና የመናህሪያ አሥተዳደር አስተባባሪ ባለሙያ ኀይለማርያም ወረታው እንዳሉት በአካባቢው የነዳጅ ማደያ ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች በጥቁር ገበያ ገዝተው ለመጠቀም ተገደዋል። በዚህም የትራንስፖርት ታሪፍ መጨመርን እንደ አንድ ምክንያት አንስተዋል። በዚህ ምክንያት ሕግን ለማስከበር መቸገራቸውን ነው ባለሙያው ያነሱት። ችግሩን ለመፍታት በወረዳው ሦስት ባለሃብቶች የማደያ ግንባታ ፈቃድ ወስደው በመገንባት ላይ መኾናቸውን አንስተዋል። እስከ 2015 ዓ.ም መጨረሻም አገልግሎት አንደሚጀምሩም ገልጸውልናል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በሊሁን የዞኑን የነዳጅ ማደያ ችግር ለመፍታት 22 ባለሃብቶች የግንባታ ፈቃድ መውሰዳቸውን ነግረውናል። ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ግንባታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን በግንባታ ሂደት ላይም ያሉ ስለመኖራቸው አንስተዋል። ወደ ሥራ ያልገቡ ስምንት ባለሃብቶች ደግሞ መነጠቃቸውን ነው የነገሩን።
ማደያዎች ተጠናቀው ሥራ እስኪጀምሩ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የነዳጅ ቸርቻሪ ነጋዴዎች በተተመነ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ መደረጉን ነው ያነሱት። በዚህም በዞኑ የነዳጅ አቅርቦት ችግር እስከ አሁን አለመፈጠሩን ኀላፊው ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ወደ ዞኑ የሚገባውን ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሌላ አካባቢ ለማሻገር ጥረት የሚያደርጉ ሕገወጦች ስለመኖራቸው ነግረውናል። ኀላፊው ባለፉት 7 ወራትም በሕገወጦች ላይ በተደረገ ክትትል ከ20 ሺህ በላይ ሊትር ነዳጅ መወረሱንና በአዘዋዋሪዎች ላይም ክስ መመስረቱን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!