“አሁን ላይ ከመደበኛ ህክምና ባሻገር ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ለልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ወረፋ እየጠበቁ ነው” ዶክተር በቀለ ዓለማየሁ

61
አዲስ አበባ :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር ከልብ ህሙማን ማዕከልና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይቱ ላይ በቀረበ ጥናት በተለይ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከፅኑ ህሙማን ውስጥ ቀዳሚዎቹ የልብ ህሙማን ናቸው ተብሏል። በጥናቱ በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ነው የተገለጸው። አሁን ላይ ከመደበኛ ህክምና ባሻገር ከ10 ሺህ በላይ ዜጎች ለቀዶ ጥገና ህክምና ወረፋ እየጠበቁ መኾኑን የዘርፉ ባለሙያ ዶክተር በቀለ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡
የልብ ህሙማን ማዕከል ፕሬዝደንቱ አቶ እንዳለ ገብሬ በበኩላቸው መንግሥት በዘርፉ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ባሻገር በግሉ ዘርፍ ቢሰራበትም የታሰበውን ያክል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ብለዋል። በተለይ ህክምናውን በበርካታ የጤና ተቋማት ማግኘት የሚቻል አለመኾኑ ጉዳዩን አወሳስቦታል ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ኢሉባቡር ቦና በሽታው በርካቶችን በፅኑ ህመም እያቆየ በመኾኑ ጤና ሚኒስቴር በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ነው ብለዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የልብ ህሙማን ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ በመንግሥትና በማዕከሉ ብቻ አጥጋቢ ሥራና ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡ ለዚህም የሚመለከተው ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ ከረመዷን ጾም እዝነትን፤ ከሁዳዴ ጾም ምኅረትን አብዝታ ትጠብቃለች፡፡
Next articleበቂ የነዳጅ ማደያ አለመኖር በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ጫና መፍጠሩን በምዕራብ ጎንደር ዞን የሚገኙ አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች ተናገሩ።