በዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች የበርበሬ በሽታን መከላከል በመቻሉ የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡

547
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) በርበሬ በኢትዮጵያውያን የአመጋገግብ ሥርዓት ውስጥ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም መነሻው የላቲን አሜሪካ ሀገራት እንደሆኑ ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ በርበሬ አምራች ለሆኑ አርሶ አደሮች ደግሞ ከምግብነት በተጨማሪ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
 
በአማራ ክልል ብዙ የበርበሬ አምራች አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳድርም በዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች በስፋት ይመረታል፡፡
 
በሁለቱም ወረዳዎች በቂ ግብዓት በመጠቀም እና እንክብካቤ በማድረግ ላይ የሚገኙት አርሶ አደሮች በ2011/12 የምርት ዘመን የተዘራውን ዘር ለመሰብሰብ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ የበርበሬ ዋጋ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየተሻሻለ መምጣት ደግሞ አርሶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ቅኝት ባደረገበት የዚገም ወረዳም አንድ ኪሎ በርበሬ በ60 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
 
አርሶ አደር ጥሩነህ ካሳሁን የዚገም ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ በተያዘው የምርት ዘመን በሦስት ሄክታር ማሳ ላይ በርበሬ ዘርተው እየተንከባከቡ ነው፡፡ 18 ኩንታል ማዳበሪያም ተጠቅመዋል፡፡ በማሳ ላይ በሚገኘው በርበሬ እስከ አሁን ከ30 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮ የዝናቡ ስርጭት ለበርበሬ ምርት እጅግ ተስማሚ እንደሆነም አጫውተውናል፡፡ ከተዘራው የበርበሬ ምርት ደግሞ እስከ 20 ኩንታል ምርት ለማገኘት ተስፋ አድርገዋል፡፡ አርሶ አደሩ የበርበሬ ሰብሉ የዛላ አያያዝ ጥሩ መሆኑን በመግለጽ ከምርቱ እስከ 300 ሺህ ብር ለማግኘት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በርበሬ አጠውልግ ወይም ስር አበስብስ ፈንገስ ምርቱን እንዳይጎዳውም የባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ በመተግበር በመከላከል ሥራ ላይ እንደሚገኙ ነው አርሶ አደሩ የተናገሩት፡፡
የዚገም ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ ብሩ በዚገም ወረዳ 8 ሺህ 289 ሄክታር ማሳ በበርበሬ ዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም 332 ሺህ 92 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በወረዳዋ 17 ሺህ 444 አርሶ አደሮች በርበሬ በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት አርሶ አደሩ የበርበሬ ምርትን በጥራት አምርቶ ይበልጥ እንዲጠቀም ተገቢ ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡ በርበሬን የሚያጠቃ በሽታን ለመከላከል አንድን ማሳ ደጋግሞ በርበሬ አለመዝራት፣ የተመረጠ ዘር መዝራት፣ የጎርፍ ማፋሰሻዎችን መሥራት እና መሰል ባሕላዊ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀማቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም እስካሁን በወረዳው በሽታው አልተከሰተም ተብሏል፡፡
 
ከክረምቱ መግቢያ ጀምሮም እስካሁን በወረዳው የተስተካከለ የአየር ፀባይና ተስማሚ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ የበርበሬ ሰብል በተሻለ ቁመና እንዲገኝ አስችሎታልም ብለዋል አቶ አሰፋ፡፡ በወረዳው የበርበሬ አምራች አርሶ አደሮች የገቢ ሁኔታም ሲታይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመጣ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
 
በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የሰብል በሽታ ተመራማሪ ዶክተር ቦጋለ ንገር የበርበሬ አጠውልግ ወይም ስር አበስብስ በሽታን ለመቋቋም የሚያስችል ዘር እስካሁን የለም ብለዋል፡፡ በሽታው አፈር ላይ በመቆየት እርጥበት ሲያገኝ እንደሚነሳ የተናገሩት ተመራማሪው ፈንገሱን ሙሉ በሙሉ መከላከል ባለመቻሉ በአማራ ክልል የሚገኙት የበርበሬ አምራች አካባቢዎች በዚህ የፈንገስ በሽታ በብዛት እንደሚጠቁም አብራርተዋል፡፡ የበሽታው መንስኤም “ፎዛሪየም አክሰስ ፎረም” የሚባል ረቂቅ ተህዋስያን መሆኑን ዶክተር ቦጋለ ነግረውናል፡፡ ፈንገሱን ለመከላከል የበርበሬውን ዘር “አፕሮን ስታር” በተባለ ኬሚካል ማሸት፣ ችግኙ ወደ ማሳ ከመዘዋወሩ አስቀድሞም “ሪዴቭል” በተባለ ኬሚካል ስሩን ነክሮ መትከል እንደሚገባ ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡ ምርምር ማዕከሉ አርሶ አደሩ በባሕላዊ መንገድ ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ዘመናዊ መከላከያ ዘዴዎችን እንዲጠቀም እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
Previous articleበኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚልና በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ከአማራና ከቅማንት ሕዝብ ከተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
Next articleየለውጥ አመራር ሰጭነት ስልጠና በባሕር ዳር እየተሰጠ ነው፡፡