በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ከ391 ሚሊዮን ብር በላይ በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ስምምነት ተፈጸመ።

43
ባሕር ዳር :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕርዳር ከተማ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ከዓለም ባንክ በተገኘ የብድርና እርዳታ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች መጠጥ ውኃና ሳንቴሽን ፕሮጀክትን ለመገንባት የውል ስምምነት ተፈጽሟል።
ውሉ የተፈጸመው በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ የበላይነት በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት እና በስድስት ተቋራጮች መካከል ነው ። ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ 391ሚሊዮን 856 ሺህ ብር ወጪ ይደረግበታል ነው የተባለው።
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) በሁለተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች መጠጥ ውኃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት በአማራ ክልል አራት ከተሞች ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት። በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚኾኑ ከተሞችም ባሕርዳር ፣ ጎንደር ፣ ደሴና ደብረ ብርሃን ናቸው ብለዋል። የአማራ ውኃና ኢነርጂ ቢሮ በአራቱ ከተሞች ላይ ውኃና ፍሳሽ ላይ እየሠራ ነው ብለዋል።
በተፈፀመው ስምምነት መሰረት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች፤ 20 አዳዲስ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ 30 አዳዲስ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ 13 ነባር የሕዝብና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ጥገና እና 20 የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፍሳሽ ማስወገጃ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ በጎንደር፣ በደሴና በደብረብርሃን ይቀጥላሉ ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ፕሮጀክቶቹ ውጤታማ እንዲኾኑ እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ተቋራጮቹ በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የባሕዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ባየ አለባቸው በከተማዋ የውኃ ፍሳሽ እና ንፁሕ መፀዳጃ ቤቶች ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶችም ችግሮችን በመቅረፍ በኩል ድርሻቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ከተማ አሥተዳደሩ ፕሮጀክቶች በተገቢው መንገድ እንዲተገበሩ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል። ፕሮጀክቶቹ እንዳይዘገዩም አስፈላጊው ገንዘብ ይለቀቃም ተብሏል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ
Next articleዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።