የኢትዮጵያ መንግሥት አጋዥ ነው ብሎ እስካመነ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያለውን እውቀት ለማካፈል ዝግጁ መኾኑን የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ።

51
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ጉዳይ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
52ኛው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ውይይት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል፡፡ በውይይቱ ላይ የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ስለሰጠው ወቅታዊ መረጃ እና ማሻሻያዎች ምስጋናውን አቅርቦ ለባለሙያዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
ጥቅምት 2/2022 (እ.አ.አ) በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት እና እርሱን ተከትሎ ጥቅምት 12/2022 በናይሮቢ ኬኒያ የስምምነቱን አፈጻጸም በሚመለከት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የሰጡት መግለጫ ተስፋ ሰጭ ነበር ያለው የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ኅብረት ስምምነቱን ዳር በማድረስ ለነበረው ሚና ላቅ ያላ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የሰላም ስምምነቱን እና እርሱን ተከትሎ የወጣውን የአፈጻጸም መግለጫ ተግባራዊ ለማድረግ እስካሁን የተወሰዱትን እርምጃዎች እንደሚያደንቅ ገልጾ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ቀጣይ እና ያልተደናቀፈ የሰብዓዊ አቅርቦት፤ የመሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።
የአውሮፓ ኅብረት በጦርነቱ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ሕግ ጥሰቶችን እና ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላትን ሚና የሚያጣራ ገለልተኛ፣ ግልጽ እና አሳታፊ ሂደት እንዲኖር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትርጉም ያለው ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ነው ያለው፡፡ የምርመራው የመጨረሻው ውጤትም በመጭው መስከረም በሚካሄደው 54ኛው የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ውይይት ላይ ይቀርባል የሚል ተስፋ እንዳለውም ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ በጦርነቱ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚያጣራ የዓለም አቀፉን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን ለማገዝ እና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ የገባችውን ቁርጠኝነት ያደንቃል ያለው ሕብረቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አስተማማኝ የሽግግር ፍትህ እና የተጠያቂነት ሂደቶች ወሳኝ ናቸው ብሏል።
የአውሮፓ ኅብረት በሽግግር የፍትህ ፖሊሲ አማራጮች ላይ በቅርቡ የተካሄደው ሕዝባዊ ምክክር እና የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሽግግር የፍትህ ማእቀፍ ቀረጻ እና ትግበራ ላይ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ድጋፍ መጠየቁን ጠቁሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አጋዥ ነው ብሎ እስካመነ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ያለውን እውቀት ለማካፈል ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡ የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ ለማድረግ ንቁ፣ ገንቢ እና ውጤታማ ትብብር ያስፈልጋልም ነው ያለው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን 2004 (እ.አ.አ.) የሽግግር ፍትህን አስመልክቶ ሲናገሩ “ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ፍትሃዊነትን ለማስፈን፣ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት እና ያጋጠሙ መጠነ-ሰፊ የመብት ጥሰቶችን ለማረም የሽግግር ፍትህ ዘላቂ እና ሙሉ ሂደት ተደርጎ ይወሰዳል” ነበር ያሉት፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአካባቢው የተከሰተውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ተቀርጸው እየተሰራ ነው።
Next articleየፈተና ጥሪ ማስታወቂያ