
ባሕር ዳር :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም እና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን የኃይል መቋረጥ ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ አስታወቁ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንዳስታወቁት በሰሜን አቸፈር፣ ሻውራ፣ ሊበን፣ ዱር ቤቴ እና መውጫ ድረስ ባሉ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው የኃይል መቆራረጥ በበለስ ማከፋፈያ ጣቢያ ትራንስፎርመሮች ላይ ችግር በማጋጠሙ ነው፡፡
የተከሰተውን ችግር ለመፍታት በተቋሙ የሚመለከታቸው የዘርፍ ሥራ አስፈጻሚዎች ያሉበት ቡድን ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ባጋጠመው ችግር እና ችግሩ በሚፈታበት ሁኔታ ላይ ከአካባቢዎቹ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት መካሄዱንም አቶ ሙላት ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሙላት ገለጻ በአካባቢው የተከሰተውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች ተቀርፀው እየተሰራ ይገኛል፡፡
ችግሩን በአፋጣኝ ለመፍታት ዳንግላ አካባቢ የሚገኘውን የማከፋፈያ ጣቢያ አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ አቅም ያለው ትራንስፎርመር ዝግጁ የማድረግ እና ትራንስፎርመሩ ለሚቀመጥበት ቦታ የመሰረት ቁፋሮ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
በአካባቢዎቹ የሚስተዋለውን የኃይል እጥረት በመካከለኛ ጊዜ ለመፍታት ከጃዊ – በለስ ስኳር ፋብሪካ ተጨማሪ ኃይል ለማግኘት ከፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉን አቶ ሙላት ገልጸዋል፡፡
አካባቢዎቹ እስከ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ባሉት ቀናት ኃይል በዳንግላ ማከፋፈያ ጣቢያ ከተጀመረው የማስፋፊያ ሥራ በጊዜያዊነት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ችግር የገጠማቸውን ትራንስፎርመሮች በአምራች ድርጅቱ እንዲጠገን በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኤክስ ዲ (XD) ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር ውል ተገብቶ ሥራ መጀመሩንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ካለው ሥራ በተጨማሪ በሻውራ አካባቢ አዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት መጀመሩን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ኀላፊው ኅብረተሰቡ እስከ አሁን ያሳየውን ትዕግስት አድንቀዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!