የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ክልላዊ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ርክክብና ሽግግር አደረገ።

130
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የ2015 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ርክክብና ሽግግር በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደሃና ወረዳ ሽማምዳን ቀበሌ ጋውሳ ተፋሰስ አደረገ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኀይለማሪያም ከፍያለው (ዶ.ር) ከአራት ሚሊየን በላይ ሕዝብን በማሳተፍ ለአንድ ወር የተከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የለሙ ተፋሰሶች ኅብረተሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጾኦ ያደርጋል ብለዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ችግር በስፋት የሚስተዋልበት አካባቢ በመኾኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተፈጥሮ ሃብት ዕቀባ ሥራው አይነተኛ አማራጭ መሆኑን ዶክተር ኀይለማሪያም ተናግረዋል ።
አርሶ አደሩ የደከመበት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ስኬታማ እንዲኾን የግብርና አመራሮችና ባለሙያዎች ኀላፊነታችን መወጣት ይገባል ያሉት ቢሮ ኀላፊው ሽግግሩ ውጤት ማምጣት የሚችለው በተግባር ተሰማርተን መፈጸም ስንችል ነው ብለዋል።
በክልላዊ የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የመዝጊያ ስነ ስርአት የተገኙት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ኀላፊ አቶ ሽታሁን አዳነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዕቀባ ስራው አሁን ካለበት የበለጠ ውጤት ማምጣት የሚያስችል እምቅ አቅም መኖሩን ተናግረዋል።
አቶ ሽታሁን አያይዘውም ማኅበረሰቡ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራውን በቅንጅት በመሥራቱ ውጤት መምጣቱን ገልጸው የተፈጥሮ ሃብት እቀባ ሥራው አርሶ አደሩ ምርት በማምረት ተጠቃሚነቱን ያሳድጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ በኅብረተሰቡ እንደ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በስፋት ይሰራል ያሉት ደግሞ የዋግህምራ ብሔረሰብ ዋና አስተዳደሪ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) የለሙ ተፋሰሶችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ ኅብረተሰቡ በበላይነት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ዋና አሥተዳዳሪው አያይዘውም በዚሁ የልማት ሥራ በዞኑ በተለያዩ የልማት ቡድኖች የተደራጁ ከ8,429 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸው ከ147 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አብራርተዋል።
በልማት ሥራው የጋራና የማሳ ላይ እርከን ስራ፣ የእርጥበት ማቆያ ስትራክቸሮችና መሰል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተከናውነዋል ሲሉ ዶክተር ስቡህ ተናግረዋል።
በዞኑ የተፈጥሮ ሃብት እቀባ ሥራው 4,927 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉንም ተናግረዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተካሄደው የበጋ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበዐቢይ ፆም እና በረመዳን ፆም ለሀገር ማሰብ
Next articleቅርሶችን በመጠበቅ እና በማልማት የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።