በኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚልና በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ከአማራና ከቅማንት ሕዝብ ከተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

212
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) ውይይቱ በጭልጋ ወረዳ ሰራባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ከሁለቱም የማኅበረሰብ ክፍሎቻቸው የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶችና ወጣቶች ታድመዋል። የኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢፌድሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦሩ ሹም ጄኔራል አደም መሃመድን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። ውይይቱ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን አብሮነት፣ አንድነትና ሠላማዊ ግንኑነት የበለጠ ለሚያጠናክር፣ ችግሮቻቻውን በሠላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ቤተሰባዊ ምክክር እንደሁነ ተነግሯል።
 
የኢፌድሪ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያ ” ሁለቱ ሕዝብ ቤተሰባዊ ናቸው፤ በቤተሰብ መካከል የተፈጠረ ችግር ቤተሰብ ካልፈታው በቀር ማንም ሊፈታው አይችልም። በግጭቱም ማንም አሸናፊ ሊሆን አይችልም። ያለፈው ላይመለስ ለዛሬና ለነገ ሠላማዊ ሂደት ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት” ብለዋል።
 
ሚኒስትሯ ከዚህ በፊት ከነበሩት ሠላማዊ ውይይቶች በተለየ መልኩ ወደ ሠላም መንገድ ሊያደርስ ያስችላል ተብሎ የታሰበ የመጀመሪያ ዙር ውይይት እንደሆነ አስረድተዋል። በቀጣይም መሠል ሠላማዊ ውይይቶችን ከሕዝብ ጋር እንደሚደረጉ ተጠቁሟል።
 
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ የተጀመረው ሠላማዊ ውይይት እንዲያብብ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
 
 
ሠላማዊ ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ከሁለቱም ወገኖች የተወጣቱ ምሥጉንና ሚዛናዊ የሀገር ሽማግሌዎች የተለያዩ ሥራዎችን ሲየከናውኑ መቆየታቸውንም አስረድተዋል።
 
ተሳታፊዎቹም የታሠሩ ሰዎች በምሕረት አዋጁ እንዲለቀቁና የተፈናቀሉ ወገኖች ዘላቂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
 
ዘጋቢ፦ ሀይሉ ማሞ
Previous articleለጉሙሩክ ደረቅ የመቅረጫ ጣቢያ ግንባታ ይፈለጋል የተባለው ቦታ ለ20 ዓመት ወደ ሥራ ባለመግባቱ በከተማው እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleበዚገም እና አየሁ ጓጉሳ ወረዳዎች የበርበሬ በሽታን መከላከል በመቻሉ የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡