”ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሀብቶች በፍጥነት እና በጥራት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው” ግርማ የሺጥላ

42
ደሴ:መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሀብቶች በፍጥነት እና በጥራት ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሺጥላ ገልጸዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በሀርቡ ከተማ አሥተዳደር አዲስ መንደር ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርክ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 46 ባለሀብቶች የቦታ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ግርማ የሺጥላ ቦታ ተረክበው ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሀብቶች በፍጥነት እና በጥራት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ከአካባቢው አሥተዳደር ጋር በመኾን የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።እነዚህ ባለሀብቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለአጠቃላይ ልማቱ በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል። አካባቢው ለወደብ ቅርብ እና ባለብዙ ጸጋ እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም ያለበት በመኾኑ አጋጣሚውን መጠቀም እንደሚገባም ነው አቶ ግርማ የገለጹት። በደቡብ ወሎ ዞን በሀርቡ ከተማ አሥተዳደር አዲስ መንደር ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ቦታ የተረከቡ አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው፡፡
ቦታውን የተረከቡ አልሚ ባለሀብቶችም በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። በመንግስት በኩል መሟላት የሚገባቸውን መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉም ጠይቀዋል።በደቡብ ወሎ ዞን በሀርቡ ከተማ አሥተዳደር አዲስ መንደር ሁለገብ ኢንዱስትሪ ፓርክ 50 ነጥብ 5 ሄክታር ስፋት ያለው ሲኾን ከአምስት ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም የሚያስችሉ ሸቀጦችን ለአባሎቻቸው እና ለማኅበረሰቡ እያቀረቡ ነው” የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ