
ባሕር ዳር :መጋቢት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች ላይ ያለውን የዋጋ ንረት እና የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እየሠሩት ያለውን ሥራ አሚኮ ተዟዙሮ ቃኝቷል።
ወይዘሮ መሠረት መኮንን ይባላሉ፡፡ በባሕርዳር ከተማ አስተዳዳር የቀበሌ 11 ነዋሪ ናቸው፡፡ ባለትዳር እና የልጆች እናት ናቸው፡፡ ኑሯቸውን የሚመሩት ደግሞ በመንግሥት ሥራ በሚያገኙት አነስተኛ ደመወዝ ነው፡፡ የጣና ጎህ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር የቁሳቁስ ሱቅ በአቅራቢያቸው ይገኛል፡፡ የሱቁ በአቅራቢያቸው መኖር የተለያዩ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ የጣና ጎህ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ጤፍ፣ ፊኖ ዶቄት፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ አጃክስ፣ ክብሪት እና ሌሎችንም ሸቀጣ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ደግሞ ለወይዘሮ መሠረት የሁልጊዜ ፍላጎቶች ናቸው፡፡ አሁን አሁን ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበሩ ባጋጠመው የገንዘብ ችግር ሁሉም ሸቀጦች በሚፈለገው ልክ እየቀረቡ አለመኾናቸውን አንስተዋል፡፡ ወይዘሮ መሠረት ከአሁን በፊት በደመወዝ የዱቤ ጤፍ ይቀርብ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ መሠረት የጣና ጎህ ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበር ሁሉንም ሸቀጥ በአግባቡ ማቅረብ ባለመቻሉ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዴ ጤፍ ከቀረበ ዘይት እና ዱቄት ይቀራል፡፡ ዘይት ከቀረበ ደግሞ ፓስታ መኮረኒ ሩዝ የመሳሰሉ ሸቀጦች አይቀርቡም፤ ይኽም ሸማቹ አባልነቱን እየተወ ወደ ነጋዴው እንዲሄድ እያሰገደደው መኾኑን አንስተዋል፡፡ ጤፍ፣ ፓስታ ማካሮኒ በቋሚነት ቢቀርቡ ሲሉም ጠይቀዋል።
ማኅበሩ ካሁን በፊት ለአባላቱ ስኳር ያቀርብ ነበር አሁን ግን ስኳር ከቀረበ 8 ወራትን አስቆጥሯል ብለዋል፡፡ መንግሥት ይሕን ችግር ለመቅረፍ ለሸማች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ንረት ሸማቹ የሚቋቋምበትን መንገድ ቢያስተካከል ሲሉም አስተያየት ሠጥተዋል፡፡ ማኅበሩ ካሁን በፊት ያቀርባቸው የነበሩ የኢዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን በአግባቡ ቢያቀርብ ሲሉም አስተያዬት ሠጥተዋል፡፡
በጣና ጎህ ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበር ሱቅ ላይ ዘይት ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ዘቢደር ደርበው በበኩላቸው ከማኅበሩ የተለያዩ አገልግሎቶችን እያገኙ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ዘቢደር ልጆቻቸውን ለማስተማር እና ቤተሠባቸውን ለመመገብ የጣና ጎህ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር የሚያቀርበው የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች ኑሮአቸውን እየደጎመላቸው መኾኑን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ዘቢደር ገቢያቸው አነስተኛ በመኾኑ ጤፍ በሁለት ወር ክፍያ ከማኅበሩ ይወስዱ ነበር፡፡ አሁን የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ በተለመደው አግባብ ተጠቃሚ መኾን አልቻሉም፡፡ ወይዘሮ ዘቢደር አባል ባይኾኑም የሚያገኙት ጥቅም ብዙ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ተጠናክሮ የሚፈለጉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአግባቡ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡም አባል በመኾን እና የሚያቀርበውን ምርት በወቅቱ በመግዛት የኑሮ ውድነቱን ሊቋቋም ይችላል ብለዋል፡፡
የማኅበሩ አባል የኾኑት አቶ ፈንታሁን ግርማ የጣና ጎህ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር በ2000 ዓ.ም እንደተቋቋመ ገልጸዋል፡፡ማኅበሩ በወቅቱ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል ታስቦ እንደተቋቋመ ተናግረዋል፡፡ የጣና ጎህ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ከስኳር እና ከዘይት በስተቀር ሁሉንም ሸቀጣ ሸቀጦች ለተጠቃሚዎች ሲያቀርብ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ማኅበሩ ለኹሉም ማኅበረሰብ እኩል አገልግሎት እየሠጠ ነው ይኽን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የጣና ጎህ ሸማቾች ኅብርት ሥራ ማኅበር ሥራ አሥኪያጅ ጌትነት አስረስ ማኅበሩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ጤፍን ጨምሮ የዋጋ ጭማሪ የሚታይባቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ እያቀረበ ነው። የሸማቾች ኅብርት ሥራ ማኅበራት ተጠናክረው መሥራት ከቻሉ እየተከሰተ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ባለበት ማስቆም ይችላሉ ብለዋል። ሥራ አስኪያጁ የገንዘብ እጥረቱና የተፈቀደላቸው ቦታ ሕጋዊ ኾኖ ወደ ሥራ አለመግባት ለሥራቸው እንቅፋት እንደኾነባቸው ጠቁመዋል።
የግዮን ሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበር ሰብሳቢ መሥፍን ፈጠነ በበኩላቸው ማኅበሩ ከኢንዱስትሪ እና የከግብርና ምርቶች በተጨማሪ የዳቦ እና የምግብ አገልግሎት እያቀረበ ነው ብለዋል። ማኅበሩ 586 አባላት አሉት፣ ምርት ቀጥታ ከፋብሪካዎች እና ከአምራቹ እየገዛ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል። በ4ዙር 400 ኩንታል ጤፍ በማምጣት ያከፋፈለ ሲኾን ለመንግሥት ሠራተኞችም የዱቤ አገልግሎት በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረጉ መኾኑን ጠቁመዋል።ማኅበሩ ከራሱ ካፒታል በተጨማሪ በባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበር ማደራጃ መምሪያ ለፈለገ ዓባይ የሸማቾች ዩኒየን በተሠጠ 20 ሚሊዮን ብር ተገዝቶ የሚቀርብን የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርት ከሌሎች ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ተካፍለው በሚደርሳቸው በጀት እየተንቀሳቀሱ መኾኑንም ጠቁመዋል።
አቶ መስፍን ማሕበሩ ከካፒታል ችግር በተጨማሪ ከአምስት ዓመት በፊት በጊዜያዊነት ያገኙትን ቦታ ሕጋዊ ዕውቅና ባለማግኘቱ ግንባታ መገንባት አለመቻሉ ሸማቹ ማኅበረሰብ የሚፈልገውን አገልግሎት እያገኘ አይደለም ብለዋል። አሁን ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሠራ ቤት አገልግሎቱን እያቀረብን ነው ነግር ግን ምርቶች በፀሐይ ሙቀት ተበላሽተው ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት እውቅና እንዲያገኝ እና ማኅበሩ የራሱን ሕንጻ ገንብቶ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲሠጥ ጠይቀዋል። ቀጣይ አባላት ከማኅበራቸው ጋር የጠነከረ ግንኙነት እንዲኖራቸው እና ምርቶችን እንዲወስዱ ማድረግ፣ አዳዲስ አባላት የማፍራት እና ካፒታል የማሳደግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነግረውናል።
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ኀላፊ ጌትነት አማረ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም የሚያስችሉ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለአባሎቻቸው እና ለማኅበረሰቡ እያቀረቡ ነው ብለዋል። ገበያ የማረጋጋት ሥራው የበርካታ አካላት ሚና ቢኾንም የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአባላት ብቻ ሳይኾን ለማኅበረሰቡም ሸቀጣ ሸቀጥ እያቀረቡ እንደኾነ አስረድተዋል። አቶ ጌትነት እየቀረበ ያለው ለኹሉም ተደራሽ ኾኗል ማለት ግን አይቻልም ብለዋል።
በክልሉ 462 የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተቋቁመው አገልግሎት እየሠጡ መኾኑንም ተናግረዋል። እነዚህ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ደግሞ 7 የሸማቾች ዩኒየን አቋቁመዋል። የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ባቋቋሙት ዩኒየንም ምርት እየቀረበላቸው መኾኑን አቶ ጌትነት ጠቁመዋል። የዋጋ መናር ችግሩን ለመቅረፍ ከሸማቾች በተጨማሪ ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲሠሩ ትስስር መፈጠሩንም አንስተዋል። በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ውይይቶች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ማኅበራቱ ምርት ከቦታ ቦታ አዟዙረው እንዲያቀርቡ የተደረገበት አግባብ መኖሩንም አንስተዋል። በተለይ ሰብል የመሰብሰብ እና እጥረት ወዳለበት ቦታ የማድረስ ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም አንስተዋል። በክልሉ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ 314 ሚሊዮን ብር ለከተማ አሥተዳደሮች ተዘዋዋሪ ብድር ተሠጥቷል ነገር ግን እስካሁን 158 ሚሊየን ብር ብቻ ነው ወደ ሥራ ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ያለው ብለዋል። ተዘዋዋሪ ብድር የሚሠጡ ከተማ አሥተዳደሮች አፈጻጸማቸው የተለያዬ መኾን የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚፈለገውን አገልግሎት ለማኅበረሰቡ እንዳያቀርቡ እንቅፋት ኾኗል ነው ያሉት። ይሕን ለመቅረፍም እየተሠራ ነው ብለዋል አቶ ጌትነት።
ኀላፊው እንዳሉት በወጥነት ሥራውን ለመሥራት እና ተደራሽ ለማድረግ የሕገወጥ ነጋዴው መበራከት አንዱ ችግር መኾኑን ጠቅሰው እርምጃ እየተወሰደ እና አሠራር እየተዘጋጀ መኾኑንም ተናግረዋል። ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። አቶ ጌትነት በክልሉ 72 ዩኔኖች ስለመኖራቸው ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 27ቱ ዩኒየኖች የገንዘብ ብድር እና ቁጠባ ዩኒየኖች ናቸው። 23ቱ ዩኒየኖች ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበር ናቸው። 7ቱ ደግሞ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር ናቸው። ቀሪዎቹ በልዩ ልዩ ዘርፍ የተቋቋሙ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
አቶ ጌትነት አመራሩም ኾነ ማኅበረሰቡ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ሚና በመለየት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በተለያዬ ጊዜ በተነሱ ጥያቄዎች ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት የተሰጠው ቦታ ሕጋዊነት እንዲያገኝ የሚመለከተው አካል እየተጠየቀ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!