
የክልሉ ሰላም ለማስቀጠል ውስጣዊ አንድነት ለማጠናከር ያስፈልጋል።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ውስጣዊ አንድነትን ማስጠበቅ ራስን ማስከበር፣ ሰላምንም ማረጋገጥ ነው፡፡ በአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ላይ በተሠራው ሥራ ክልሉ የተረጋጋ እንዲኾን ማድረጉ መቻሉ ተገልጿል፡፡ ክልሉ የተረጋጋ እንዲሆን ደግሞ የጸጥታ ኀይሎች እና የሕዝቡ ቅንጅት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ከአሚኮ ኦንላይን ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለፉት ዓመታት ለተከታታይ ጊዜ ግጭት፣ መፈናቀል፣ ሞት እና የንብረት ውድመት ሲደርስ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ ከሕዝብ አንድነት ይልቅ በሕዝብ መለያየት እና በንፁሐን ደም የሚነግዱ በመኖራቸው የሚነሳ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የሕዝብን አንድነት እና አብሮነትን የማይፈልጉ ኀይሎች ግጭት ሲያሴሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ በአንድነት ዘመናትን ያሳለፈ እና ችግሮችን በጋራ ያለፈ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የብሔር፣ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ጽንፈኝነት መኖር ለሰላም ጸር እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡ የኢኮኖሚ እና የስልጣን ሽኩቻ ላይ የሚጥሩ ኀይሎች አካባቢውን እንደሚጠቀሙበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡ በሕዝብ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች መኖር ለአካባቢው ማኅበረሰብ አብሮ መኖር ተግዳሮት ሆኖ መቆዬቱንም ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለአብነት ያነሱት ኀላፊው፤ ግጭቱ የተነሳው የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት በሚጥሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የግል ጥቅማቸው ላይ የሚያተኩሩ አካላት የጋራ ጉዳዮች እንዲጠነክሩ ከማድረግ ይልቅ ግጭት እንዲፈጠር እንደሚሠሩም አንስተዋል፡፡ ጥላቻን በመጎሰም ማኅበረሰቡ በሀገሩ ተረጋግቶ እንዳይኖር፣ ዋስትና እንዳይኖረው እና ሃብት አፍርቶ እንዳይኖር የሚያደርግ ነውም ብለዋል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ በጥርጣሬ እንዲነሳና ወደ ብሔር ግጭት እንዲሄድ የሚፈልጉ ኀይሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው ያለ መሪ ከራስ በላይ ለሕዝብ አልሞ በመሥራት፣ ግራ ቀኙን አጥፊ በተደራጀና በመረጃ ላይ ተመስርቶ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ ሲችል ችግሮች በዘላቂነት እንደሚፈቱም ገልጸዋል፡፡ በውስጡ የአመራር ችግር፣ የቡድንተኝነት ስሜትና ጽንፈኝነት ካለ የሕዝብ አንድነትን የሚያሻክር ነገር እንደሚከሰት አይተናልም ብለዋል፡፡ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ትልቁ ኀላፊነት እና ቁልፉ ጉዳይ የመንግሥት መዋቅር ገለልተኛና ነጻ ሆኖ ሲያገለግል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ነጻና ገለልተኛ አገልግሎት ለመስጠት ራስን ማሳመን ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተፈጥሮ የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሕዝብ ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ በውይይታቸው ችግሮች እንዲቀረፉ መዋቅራችሁን አጥሩ የሚል ሃሳብ ከሕዝቡ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በየደረጃው ያለ የመንግሥት መዋቅር ስለ ሕዝብ አንድነት እና እሴት የሚያስብ፣ ነገን የሚያይ እንዲሆን ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡ መዋቅርን ማጥራት፣ የሕዝብን እሴት መሠረት ያደረገ መሪ ማፍራት፣ ሕዝባዊ አመኔታ ያለው መሪ መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ ከፈተና እንዲወጣ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡ በችግሩ ላይ አካባቢያዊ መፍትሔ እንዲያቀርብ የሚያስችል ውይይት እያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በጅምሩ የተገኘው ውጤትም ቀላል የሚባል አለመሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ ሕዝቡ መረጃ በመስጠት ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር እየተባበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰፋፊ የንቅናቄ መድረኮች እየተደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን አጋልጦ የሕግ የበላይነትን ያረጋግጣልም ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድለት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡
በተሠራው ብርቱ ሥራ የአማራ ክልል የተረጋጋ እንዲሆን መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገውን ማድረግና በተቋሙ ሊሠሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ሰላምና ደኅንነትን ለማስከበር ወሳኝ ናቸውም ብለዋል፡፡ የጸጥታ መዋቅሩ ሥርዓታዊ እና ሥነ ምግባራዊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥት ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ የወሰደው ቁርጠኝነት ትልቅ ነውም ብለዋል፡፡
የጸጥታ መዋቅሩ እንዲጠናከር የተሠራው ሥራ አበረታችና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ሕዝብን መሠረት ያደረገ ሥራ መሥራት ለሰላምና ጸጥታ ሥራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ ከሰላም የሚገኘው ፋይዳ ትልቅ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ ሰላም ሲኖር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንደሚጨምርም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ከተሞች ሰላምና ደኅንነታቸው እየተጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ውስጣዊ አንድነት፣ የአስተሳሰብ አንድነት እና የልማት ፍላጎት ሊኖር ይገባልም ነው ያሉት፡፡ የውጩን ተጽዕኖ የምንቋቋመው የውስጥ ሰላም እና የውስጥ አንድነት ሲኖር ነውም ብለዋል፡፡ በመለያየት የምናመጣው ፋይዳ የለም፣ በመለያየት ለችግሮች ተጋላጭ ነው የምንኾንም ነው ያሉት፡፡ ሰላምና ጸጥታን ማስጠበቅ ልማት እንዲፋጠን ያደርጋልም ብለዋል፡፡
በክልሉ ተስፋ ሰጪ መደማመጥ እንዳለ የገለጹት ኀላፊው፤ ለመደማመጡ እንቅፋት የሚኾኑ ሀገራዊ አለመረጋጋት እና የፖለቲካ አለመስከን እንዳለም ገልጸዋል፡፡ የምንሻገረው ድልድይ ረጅም ቢኾንም መሻገራችን ግን አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!