አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር ርዕሰ መሥተዳድር ኾነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

263
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መሥተዳድር አድርገው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ርዕሰ መሥተዳደሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥ እና አካታች የኾነ አሥተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈፃሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት የተጣለባቸው መኾኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀፅ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፤ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማቆም በፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት አንቀጽ 10(1) መሠረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም በማስፈለጉ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጋቢት 9፣2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አሥተዳደር ደንብን አፅድቋል።
በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሠረት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አመረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleደብረብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ተደረገ።
Next article“በአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ላይ በተሠራው ሥራ ክልሉ የተረጋጋ እንዲኾን ማድረግ ተችሏል”የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሰላኝ ጣሰው