
የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት መምሪያ ደግሞ ችግሩ የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን መሆኑን ገልጧል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 25/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ደግሞ ችግሩ የተፈጠረው ኮሚሽኑ ደረቅ የመቅረጫ ጣቢያ መገንባት ሲገባው ከተግባር እና ኃላፊነቱ ውጭ ደረቅ ወደብ ለመገንባት በወቅቱ በአካባቢው ከሥራ ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩ እንደሆ አስታውቋል፡፡ ውይይቱም በሕጋዊ መንገድ በሰነድ የተደገፈ ሳይሆን በቃል ብቻ መሆኑ ሌላኛው ችግር እንደሆነ ኮሚሽኑ ገልጧል፡፡
የመተማ ዮሐንስ ነዋሪዎች እንደገለጹት መንግሥት ከሁለቱ ሀገራት ድንበር (ኢትዮጵያና ሱዳን) በመነሳ በተለምዶ ገብርኤል እየተባለ እስከሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን አንድ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ቦታ ከ1991 ጀምሮ ለልማት ጠይቆ ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት ለመቅረጫ ጣቢያ ግንባታ ይፈለጋል የተባለው ቦታ ለ20 አመት ፕላን ሳይሰራለት ቆይቷል፡፡ ማኅበረሰቡም ለታለመለት ዓላማ ይውላል በሚል አካባቢውን ማልማት የሚያስችል አቅም እያለው ያለምንም ልማት እንዲኖር ተደርጓል ብለዋል፡፡ “ማስተር ፕላኑ” ተግባራዊ ባለመደረጉ የውኃ፣ መብራት፣ መንገድ እና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ለማሟላት እና ወደ ግንባታ ለመግባት እንዳስቸገራቸው ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡
አካባቢው የልማት እና የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ቢሆንም በልማት ስም ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ባለመደረጉ በከተማው እድገት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው ነዋሪዎች የነገሩን፡፡ ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጠዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሆነዓለም አሻግሬ እንደተናገሩት ለጉሙሩክ ደረቅ ጣቢያ ግንባታ የተጠየቀው ቦታ ተግባራዊ ባለማደርጉ በከተማው እድገት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ከሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ጀምሮ በተለምዶ ገብርኤል ተብሎ ወደ ሚጠራው አካባቢ ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ቦታ ለልማት ይፈላጋል ተብሎ አካባቢው ፕላን ሳይሰራለት ቆይቷል፡፡ 2 ሺህ 544 ቤቶችን ለማስነሳትም 197 ሚሊዮን ብር ግምት ለጉሙሩክ ኮሚሽን ቀርቧል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ነዋሪው እንዳያለማ ተደርጎ ከቆየ በኋላ ተቋሙ ግምቱን መክፈል እንደማይችል እና 10 ሄክታር መሬት ግምት ተሰርቶ እንዲቀርብለት ኮሚሽኑ እንደጠየቀ አቶ ሆነዓለም ገልጸዋል፡፡ የተሰጠው 10 ሄክታር ቦታ ለግንባታ ምቹ ባለመሆኑ ተጨማሪ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ 2 ነጥብ 3 ሄክታር መሬትም በተጨማሪነት መሰጠቱን አቶ ሆነዓለም ነግረውናል፡፡
የተጠየቀው ተጨማሪ ቦታ ለመቅረጫ ጣቢያው ከተፈቀደላቸው ቦታ ውጭ በመሆኑ የፕላን ማስተካከያ እንዲደረግ ለክልሉ ከተማ ልማት ቢሮ እና ለፕላን ኢንስቲቲዩት መቅረቡን ነው አቶ ሆነዓለም የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ስዋህሊ አቡ እንደተናገሩት ችግሩ መኖሩን አምነው፤ ከተማ አስተዳደሩ ለግንባታ ቦታ ያደረገውን ጭማሪ ቢሮው እንደማያውቀው ግን ገልጸዋል፡፡ መረጃው እንደደረሰም ምላሽ እንደሚሰጥ ነው አቶ ስዋህሊ የገለጹት፡፡ ከፕላኑ ውጭ የነበረውን የግለሰቦችን ቦታም ባለፈው ዓመት ክልሉ ፕላሉን አስተካክሎ ማጽደቁንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ፕሮጀክት መሀንዲስ ኢንጅነር ጌታሁን አባተ እንደገለጹት ደግሞ ለመገንባት የታቀደው “የደረቅ ወደብ” ግንባታ የኮሚሽኑ ተግባር እና ኃላፊነት ባለመሆኑ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት ሆኗል፡፡ ችግሩንም ለመፍታት በኮሚሽኑ ስልጣን ሊገነባ የሚችል እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በአንድ ቦታ ላይ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት “አንድ አለቅ” ወቆጣጠሪያ ጣቢያ ለመገንባት 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ ተጠይቋል፡፡ የሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሥራ እስኪጀመር ኮሚሽኑ በጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ገብቶ የኮንትሮ ባንድ ሥራዎችን ለመከላከል የሚያስችል ግንባታ ለመገንባት 10 ሄክታር መሬት የግንባታ ቦታ ቅድሚያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ይሁን እንጅ በኮሚሽኑ የተጠየቀው ቦታ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት በደብዳቤው በግልጽ ባለመገለጹ በከተማ አስተዳድሩ የተሰጠው ቦታ የመሬት መንሸራተት እና የአፈር ክለት ያለበት መሆኑ ለግንባታ አስቸጋሪ አድርጎታል፤ ችግሩንም ለመፍታት የከተማ አስተዳድሩ የማስተር ፕላን ክለሳ አድርጎ ቦታውን ለማስረከብ ጊዜ ወስዷል ብለዋል ኢንጅነር ጌታሁን፡፡
ከተማ አስተዳድሩ የፕላን ማስተካከያውንም ለኮሚሽኑ እንዳሳወቀ ወደ ሥራ እንደሚገባም ነግረውናል፡፡
የመቆጣጠሪያ ጣቢያው ግንባታ በምሥራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) የሚሠራ ነው፡፡
መቅረጫ ጣቢያው ቢሮን ጨምሮ ወደ ሀገር የሚገቡ እና የሚወጡ ምርቶችን መቆጣጠር የሚያስችሉ ለተሽከርካሪ መፈተሻ የሚያገለግል 37 ሜትር የሚረዝም መፈተሻ ማሽን፣ የምድር ሚዛን፣ ተሽከርካሪ ፓርኪንግ እና ሌሎች አገልግሎቶች ይኖሩታል፡፡
ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሰራ