
ባሕር ዳር :መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማኅበር የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው እንደገለጹት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረብርሃን ከተማ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች የመጠለያ፣የአልባሳትና የምግብ ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
በከተማው በ6 መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማኅበር በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ምግብ ነክና ሌሎች ግብዓቶችን ለተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በዚህ ዙር ሰሞኑን ተፈናቅለው ከመጡት ውስጥ 2 ሺህ 5 መቶ ለሚሆኑ የቤተሰብ ኀላፊዎች ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው 370 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና 1 ሺህ 225 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ ዳምጠው አሳውቀዋል፡፡ማኅበራቸው ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በቀጣይም ለተፈናቃዮች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋየ በየነ በበኩላቸው እንደገለጹት ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቃዮች ወደ ከተማው ገብተው በአራት የሕዝብ መገልገያ አዳራሾች እየኖሩ እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡ ወደ ከተማው የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ጠቁመዋል፡፡ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመጡ እና አሁን ደግሞ ከአዲስ አበባ እና ገላን የተፈናቀሉትን ጨምሮ 30 ሺህ የሚሆኑ ወገኖች በ6 መጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በተለይም በአንደኛው መጠለያ ካምፕ ብቻ ከ15 ሺህ የማያንሱ ተፈናቃዮች ከደረጃ በታች ተጨናንቀው እንደሚኖሩ አመልከተዋል፡፡በቅርቡ ደግሞ አዲስ ተፈናቃዮች ወደ ከተማው እየመጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው አሁን ላይ ከተማው ማስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ መሆኑን ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡
ከተማው 6 ነጥብ 5 ሄክታር ቦታ ለተፈናቃዮች ካምፕ መስሪያ ቦታ ቢያዘጋጅም ከብዛታቸው አንፃር ችግሩን መቅረፍ እንደማይችል አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በፊት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ድጋፍ ለተፈናቃዮች ያደርጉ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በመቆሙ ብዙዎች ለተደራራቢ ችግር መጋለጣቸውን አስታውቀዋል፡፡በዚህ ወቅት ከነዚህ ወገኖች ጎን መቆም የሁሉም አካላት ኃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙ አካላት ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጊዜያዊነትም ሆነ በዘላቂነት የተፈናቃዮቹ ችግር እንዲፈታ ከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እየሰራ መሆኑንም አቶ ፀጋየ ገልጸዋል ሲል የዘገበው የደብረብርሃን ከተማ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!