
ባሕር ዳር:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በእናቶችና ሕጻናት ላይ ያተኮረ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ መነሻ የዳሰሳ ጥናት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
ጥናቱ እ.ኤ.አ በነሀሴ 2018 የጸደቀውን የምግብና የሥነ ምግብ ፖሊሲ ለማስፈጸም አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።
በዛሬው ዕለት የዳሰሳ ጥናቱ በአዲስ አበባ ይፋ ሲደረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮችና አጋር አካላት ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን መሰረት እስከ 2030 መቀንጨርን ለማስቀረት በተጀመረው ሥራ በ240 ወረዳዎች አበረታች ሥራ እያከናወነች ነው።
ኢትዮጵያ በፈረንጆች 2018 ያጸደቀችውን የምግብና ስርዓተ ምግብ ፖሊሲ ለማስፈጸም ከሰቆጣ ቃል ኪዳን በተጨማሪ ከ2021 እስከ 2030 የሚቆይ የአስር ዓመት ስትራቴጂ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም የዜጎችን በተለይም የሕጻናትና እናቶችን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል የሚያስችል የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ መነሻ የዳሰሳ ጥናት ይፋ መደረጉንም ገልጸዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ መሪ ተመራማሪ ዶክተር ማስረሻ ተሰማ፤ ከትግራይ ክልልና አንዳንድ የጸጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች በስተቀር ሁሉም አካባቢዎች በጥናቱ ተካተዋል ብለዋል።
በጥናቱ መሰረት በኢትዮጵያ የሕጻናት የአመጋገብ ሁኔታ (ደጋግሞ መመገብ) እንደ ክልሎቹ የተለያየ ቢሆንም በጥቅሉ ዝቅተኛ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የሕጻናት የምግብ ደህንነት 47 በመቶ መሆኑን ገልጸው፤ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብም ከፍያለ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ የሚመገቡ ሕጻናት ቁጥርም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ችግሩን ለመፍታት ወሳኝ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የሕጻናት መቀንጨርን እስከ 2025 በ40 በመቶ ለመቀነስ የተጀመረው ጥረት ጥሩ ተስፋ የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
በጀት መመደብ፣ በጋራ የትብብር የተቀናጀ የምግብና ሥርዓተ ምግብ መረጃ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም አፈፃፀሙን መከታተል ግቡን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!