
ደብረ ብርሃን:መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የከተሞች የትብብር መድረክ በደብረብርሀን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የመድረኩ ዓላማ የከተሞችን አቅም የሚገነቡ የሀገር ውስጥና የውጭ ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት እና የተሻሉ ተሞክሮዎች የሚሸጋገሩበት ነው፡፡ በመድረኩ ከኢትዮጵያ ከተሞች የተገኙ ከንቲባዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጸጋዬ በየነ ደብረብርሃን ከተማ በቱሪዝምና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ምቹና ተመራጭ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል።
ደብረብርሃን ከተማ በልዩ ልዩ የልማት ሥራ ለሚሳተፉ ባለሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት የምትሰጥ በመሆኗ የአልሚዎችን ቀልብ እየሳበች መሆኗንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አንዷለም ጤናው የከተሞች ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እያደገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ መድረኩ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለባለሃብቶችም ተመራጭ እንዲሆኑ ከአቅም ግንባታ ጀምሮ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ እና ተሞክሮዎችን በማሸጋገር የከተሞችን ዕድገት የሚያፋጥኑ ስልጠናዎቸ የሚሰጡበት የትብብር መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።
በዕለቱ አዲሱ የከተማ ቤቶች ልማት ስትራቴጂ የሚቀርብ ሲሆን ሌሎች ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የድርጊት መርሐግብሩ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!