የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኢትዮጵውያን የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል መሪ ዕቅድ እና ረቂቅ ፖሊሲ አስተዋወቀ፡፡

952

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) መንግሥት ለማዕድንና ነዳጅ ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠቱን የኢፌዴሪ ማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የማዕድን እና ነዳጅ ዘርፍ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት እና የኢንዱስትሪ ግብዓት በማቅረብ በኩል ከፍተኛ ተስፋ ከሚጣልባቸው መስኮች አንዱ ነው፡፡ ወርቅ፣ ኤመራልድ፣ ኦፓል እና ሳፋየር እንዲሁም የተፈጥሮ ጋዝ በኢትዮጵያ በስፋት ከሚገኙ የማዕድናት እና ነዳጅ ሀብቶች መካከል እንደሆኑም የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዲፕሎማት ማኅበረሰብ አባላት፣ ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ከዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ ከሚኒስትሮች እና ከክልል ማዕድን ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በዘርፉ ቁልፍ ችግሮች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ መክሯል፡፡

ሊያሠራ የሚችል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አለመኖር፣ የካፒታል እጥረት፣ በዘርፉ የካበተ ዕውቀት እና የተደራጀ ሥነ ምኅዳራዊ መረጃ አለመኖር ዋና ዋና ችግሮች ሆነው ቀርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በዚህም የተነሳ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አለማግኘቷን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የዘርፉን አዋጭነት በመረዳት ሊያሠራ የሚችል ፖሊሲ እና ስትራቴጀ ቀረጾ ሥራ ላይ ለማዋል በሂደት ላይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሚስተር ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸዉ በአህጉሩ የሚገኘዉን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ለማወቅ እና ጥቅም ላይ ለማዋል ክህሎትን ማሳደግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ “ያለንን ሀብት በራሳችን አቅም ወደ ጥቅም የመቀየር አቅሙ አለን፤ በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት የተሻለች ናት” ብለዋል፡፡ ለውጤታማነቱም ባለሙያዎችን ማሰልጠን እና ማብቃት እንደሚገባ ነው የመከሩት፡፡ መንግሥትም ዘርፉን ለማሳደግ በተለይም ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ቆራጥ መሆን እንዳለበት ሚስተር ቬራ መክረዋል፡፡

በዛሬው ውይይት የዘርፉ የቀጣይ 10 ዓመት መሪ ዕቅድ እና ረቂቅ ፖሊሲ ቀርቦ ተመክሮበታል፡፡ የማዕድን እና ነዳጅ ዘርፍ እስካሁን ከአጠቃለይ የሀገሪቱ ገቢ ድርሻው 1 በመቶ ብቻ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ እስከ ቀጣይ 10 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ 10 በመቶ ድርሻ እንዲኖረ ለማድረግ እንደታቀደም ተመላክቷል፡፡ በዚህም ከዘርፉ 20 ቢሊዮን የሜሪካን ዶላር ለማግኘት ነው የታቀደው፡፡ ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኢትዮጵውያን የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደታሰበም በቀጣይ 10 ዓመት መሪ ዕቅድ እና ረቂቅ ፖሊሲው ላይ ተመላክቷል፡፡

ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ – ከአዲስ አበባ

Previous articleየሰቆጣ ከተማ ሕዝብ የንፁህ መጠጥ ውኃ ጥያቄ አሁንም ምላሽ አለማግኘቱን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleለጉሙሩክ ደረቅ የመቅረጫ ጣቢያ ግንባታ ይፈለጋል የተባለው ቦታ ለ20 ዓመት ወደ ሥራ ባለመግባቱ በከተማው እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡