
ችግሩን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዘላቂነት ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ክልሉ ገልጿል፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሰቆጣ ከተማን የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ከወለህ ወንዝ ለመሳብ ጥናቶች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መገባቱን የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በውኃ ፓምፕ መቃጠል ምክንያት ሰቆጣ ከተማ ላይ የንፁህ መጠጥ ውኃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ የውኃ ፓምፑ ቢኖርም ተራ ለማግኘት እስከ ሦስት ሳምንት እንደሚጠብቁ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ወርቅነሽ ተገኘ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ሰቆጣ ከተማ ውስጥ በየዓመቱ የንፁህ መጠጥ ውኃ ጥያቄ ያልቀረበበት ጊዜ እንደሌለ የተናገሩት ወይዘሮ ወርቅነሽ ‹‹ከዛሬ ነገ ይሻላል›› ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ምንም ለውጥ ባለመኖሩ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሦስት ልጆች አሉኝ›› ያሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ የልጆቻቸውን የግል ንፅህናቸውን ጠብቆ፣ የሚጠጡትን ውኃ ለማቅረብ እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡
ችግሩ በምግብ ቤቶች ላይ የከፋ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ወርቅነሽ ‹‹መንግሥት በየዓመቱ ምሬታችን ጋር እንድንኖር ካልፈለገ ዘላቂ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዞ እንዲፈታልን እንፈልጋለን›› ብለዋል፡፡
“የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ የውኃዋ አገልግሎት እናገኛለን ብየ በማሰቤ ለቤተሰቦቼ በቀን እስከ 100 ብር እያወጣሁ የታሸገ ውኃ ስሰጥ ነበር፤ ችግሩ የፀና በመሆኑ ግን የጉድጎድ ውኃ አፍልቶ መጠጣትን አማራጭ አድርጌያለው” ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሞገስ ስዩም ናቸው፡፡
ሰቆጣ ከተማ ላይ ያሉት የውኃ ጉድጎዶች ውስን በመሆናቸው ውኃ ለማግኘት ረጃጅም ስልፎችን ጠብቆ በትዕግስት ውኃ መቅዳትን እንደሚጠይቅ የተናገሩት አቶ ሞገስ ብዙ የሥራ ጊዜያቸውን ውኃ በማምጣት እና ቤት በመጠበቅ እንዲያሳልፉ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የሰቆጣ ከተማ ከንቲባ አቶ በኃይሉ መኮንን ‹‹ችግሩ ለዘመናት የነበረ ነው›› ብለዋል፡፡ በአካባቢው በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የውኃ እጥረት እና የውኃ ፓምፕ በመቃጠሉ ለሁለት ሳምንት ሙሉ በሙሉ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦቱ መቋረጡንም አስታውቀዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ከአማራ ክልል የውኃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ እና አውስኮድ ጋር በመተባበር የተቃጠለውን የውኃ ፓምፕ ከጉድጎዱ በማውጣት በሌላ እንዲተካ እያደረጉ እንደሆነም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የተወሰደው መፍትሔ እስከ ዛሬ ያጋጠመውን ችግር ይፈታል፤ ጉድጓዱ ውኃ ለማጠራቀም ጊዜ ይወስዳል፤ በቂ ውኃ መያዙ ከተረጋገጠ ግን እንደተለመደው በ20 እና 25 ቀናት ውስጥ በተራ የማድረስ ሥራ ይሠራል እንጂ ችግሩን በዘላቂነት አይፈታውም›› ብለዋል፡፡
ችግሩን ለማቅለል ግን የአዲስ ፓምፕ ተከላው ከተጠናቀቀ በኋላ ‹‹ሌሎች ሁለት የውኃ ጉድጓዶች ሥራ እንዲጀምሩ የመጡት የውኃ ማውጫ ተሸከርካሪዎች ሥራቸውን ይቀጥላሉ›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በ55 ሚሊዮን ብር በአውስኮድ አማካኝነት እየተሠራ የሚገኘው የውኃ ፕሮጀክት በቅርብ ወራት ውስጥ ሥራ ይጀምራል ብለው እንደሚምኑም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ጉድጎዶች አራት ሊትር በሰከንድ ብቻ ያፈልቁ ነበር፤ አሁን እየተገነባ ያለው ደግሞ 21 ሊትር በሰከንድ ያፈልቃል፤ ያም ሆኖ በ25 ሊትር በሰከንድ ውሃ በማፍለቅ የከተማዋን ችግር ማቃለል ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
በከተዋማ ሚካኤል ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ባለፉት ሦስት ዓመታት የምንጭ ውኃ ሲጠቀሙ ነበር፤ ይህን ችግር መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፈትተውታል፡፡ በትራንስፈርመር እጥረት ሥራ አቁሞ የነበረውን የውኃ ተቋም በቅርቡ ትራንስፈርመር በመተከሉ ዜጎቹ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚሠራም ታውቋል፡፡
‹‹በሰቆጣ ከተማ ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ይገኛሉ›› ያሉት አቶ ብኃይሉ ለእነዚህ ዜጎች የሚሆን ዘላቂና በቂ የውኃ አቅርቦት ለመፍጠር ግን በዙሪያዋ ካሉ ትልልቅ ወንዞች ለመሳብ የክልሉ መንግሥት በዕቅድ ይዞ መሥራት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ምክትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አደም ወርቁ ‹‹የሰቆጣ ከተማ ውኃ እጥረት ችግር ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያ የጉድጓድ ውኃ ቁፋሮዎችን ብናደርግም በቂ ውኃ ማግኘት አልቻልንም›› ብለዋል፡፡ ዘንድሮ የተከሰተው የውኃ እጥረትም ከዚህ ጋር በተያያዘ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
‹‹በውኃ ጉድጎድ ቁፋሮ የሰቆጣ ከተማን ዘላቂ የውኃ እጥረት መፍታት እንደማይቻል በጥናት አረጋግጠናል›› ብለዋል አቶ አደም፡፡
ለዓመታት አብሮ የሚኖረውን የሰቆጣ ከተማ ውኃ እጥረት ለመፍታት ዓመቱን ሙሉ ከሚፈሰው የወለህ ወንዝ ለመሳብ ጥናቶች ተጠናቅቀው ሥራ መጀመሩን የቢሮው ምክትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አደም ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ወለህ አካባቢ ለጉድጎድ ውኃ ቁፋሮ የተዘረጉ መስመሮችን በመጠቀም ከአንድ ዓመት በላይ በማይወስድ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ጊዜው ከዚያ በላይ ጥቂት ወራትን የሚወስድ ቢሆን እንኳ ለዘላቂ መፍትሔ በመሆኑ ሕዝቡ እንዲታገስ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ