
ባሕር ዳር:መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነባትና ጠንካራ ሀገር ለማድረግ የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በፌዴራል ተቋማት ስር ለሚገኙ የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ክፍል፣ የውስጥ ኦዲት አገልግሎት፣ የሕግ አገልግሎት እና የተቋማት ለውጥ ሥራ አመራር ኃላፊዎች በቢሾፍቱ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
ምክትል ኮሚሽነሩ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ሙስና ሀገሪቱ ላይ ጫና እየፈጠሩ ካሉ ችግሮች ዋነኛው ነው ብለዋል።
ችግሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት በመሆኑ መንግሥት ሙስናን ለመታገል ብሄራዊ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን አውስተዋል።
ባህሪውን እየቀያየረ ያለውና በተለያዩ ስልቶች እየተፈጸመ ያለው ሙስና የኢኮኖሚ እድገትን በመግታት፣ የሀገር እንድነትን በማናጋት የተረጋጋ ሥርዓተ መንግሥት እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነባትና ጠንካራ ሀገር እንድትሆን የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ለጸረ ሙስና ትግሉ ስኬት በየተቋማቱ ያሉ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀው፤ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
