
ባሕር ዳር:መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠላት የሚሮጥላቸው፣ ምሽግ የሚፈራርስላቸው፣ ድል የማይለያቸው፣ ብልሃት የማይርቃቸው፣ የጦር ጥበብ የተቸራቸው፡፡ እንደ አንበሳ የጀገኑ፣ እንደ ነብር የፈጠኑ፣ ጎራዴያቸው የሠላ፣ ጀበርናቸው የመላ፣ ጦራቸው የማይስት፣ ጥይታቸው የማይወሰልት ጀግና፡፡ በምሥራቅ የመጣውን ቀጡት፣ በሰሜን የመጣውን እንዳልነበር አደረጉት፣ በደቡብ ያቆበቆበውን አደብ አስገዙት፣ በምዕራብ የተነሳውን እጅ አስነሱት፡፡ ድል ቁርሳቸው፣ አሸናፊነት መለያቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያን የነካውን ቀጡት፣ ወሰኗን ያለፈውን በእሳት ላንቃ ገረፉት፣ በሰላው ጎራዴያቸው ሸለቱት፣ በሾለው ጦራቸው ወጉት፣ በግርማቸው ጣሉት፣ በክንዳቸው ደቆሱት፤ ሠንደቋን የተዳፈረውን ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ጨረሱት፡፡ ለኢትዮጵያ ፍቅር በረሃውን ቻሉት፣ አሜካላውን አለፉት፣ በሞት መካከል ተመላለሱበት፣ የጥይት አረሩን፣ የጎራዴ ስለቱን ናቁት፣ ስለ ክብሯ ሲሉ መከራና እንግልቱን ረሱት፡፡
ስለ ፍቅሯ ተራቡላት፣ ስለ ፍቅሯ ተጠሙላት፣ ስለ ፍቅሯ ከጫፍ ጫፍ ተንከራተቱላት፣ ከጣላቶቿ ጋር ተናነቁላት፣ ስሟን እያነሱ፣ ሠንደቋን እያወሱ ምሽግ ውለው ምሽግ አደሩላት፣ ከአንቺ በፊት እኔን ያድርገኝ እያሉ ቀደሙላት፡፡ ዝናብ መታቸው፣ በረሃው ገረፋቸው፣ አሜካላው ወጋቸው፣ ድካሙ በረታባቸው፡፡ ዳሩ አብዝተው ይወዷታል፣ ከነብሳቸው አስበልጠው ይሳሱላታልና ሁሉንም ስለ ኢትዮጵያ ፍቅር ብለው ረሱት፣ ናቁት፡፡
አንደበት ቢኖራቸው የሐረርጌ ጎዳናዎች ይመሰክሩላቸዋል፣ ልሳን ቢኖረው የኦጋዴን በረሃ ስማቸውን እያነሳ ይናገርላቸዋል፣ ለወጣ ለወረደው፣ ለመጣ ለሄደው ታሪካቸውን ይዘክርላቸዋል፤ የአምባላጌ ምድር አረገደላቸው፣ ጠላት ተርበደበደላቸው፣ ወገን አደነቃቸው።
የኢጣልያን ጦር በአምባላጌ አናት ደመሰሱት፣ በመቀሌ አስጨነቁት፣ በዓድዋ ተራራ ላይ ከእግራቸው ሥር ጥለው የማትደፈር ሀገር፣ የማትረክስ አድባር፣ ጎዳናዋ የማያረማምድ ምድር እንዳላቸው አሳዩት።
መነሻቸው ከካህናት እና ከነገሥታት ወገን ነው፡፡ እናታቸው የሸዋው ንጉሥ የሣሕለ ሥላሴ ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅ ይባላሉ፡፡ አባታቸው የዶባና የመንዝ ባላባት ደጅ አዝማች ወልደ ሚካኤል ወልደመለኮት ይሰኛሉ፡፡ እነዚህ ጥንዶች በተወደደች ቀን በግንቦት አንድ 1844 ዓ.ም ወንድ ልጅ ተሰጣቸው፡፡ ስማቸውንም መኮንን አሏቸው፡፡ በአባትና በእናታቸው ቤትም በግርማና በሞገስ አደጉ፡፡ የአጼ ኃይለ ሥላሴ አባት፣ የምኒልክ ታማኝ፣ ኢትዮጵያን አብዝተው ወዳጅ ናቸው ራስ መኮንን፡፡
በዘመኑ የንጉሥ ሳሕለ ሥላሴ የልጅ ልጅ፣ የንጉሥ ኃይለ መለኮት ልጅ እምዬ ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ ሆነው ነበር፡፡ ደጅ አዝማች ወልደ ሚካኤልም ልጃቸው መኮንን 14 ዓመት በሆናቸው ጊዜ መኮንን ያሉትን ባለ ግርማ ልጃቸውን ወደ እምዬ ምኒልክ ወስደው ይህ ልጅ ከእርሶ ጋር በቤተ መንግሥት ይደግ ሲሉ ሰጧቸው፡፡ ምኒልክም እኒያን ደመ ግቡ ብላቴና በደስታ ተቀበሏቸው፡፡ በቤተ መንግሥትም አሳደጓቸው፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ብልህ ነበሩና ምኒልክ ባለሟል አደረጓቸው፡፡
ምኒልክ እኒያን ብላቴና በልዩ ልዩ ሥራ እየሾሙ ፈተኗቸው፡፡ ለዙፋናቸው ታማኝና ትጉህ አገልጋይ መሆናቸውን ተረዱ፡፡ በለጋ ዕድሜያቸው የባላንባራስነት ማዕረግ ሰጧቸው፡፡ በትጋታቸውና በታማኝነታቸው መኮንን፣ መኮንን ይባሉ ጀመር፡፡ በቤተ መንግሥት ስለ እርሳቸው የሚያወራው በረከተ፡፡ ታማኝነታቸው እና ትጋታቸው ተወደደላቸው፡፡ እምዬ ምኒልክ የግዛት አንድነትን እያረጋገጡ፣ ሥርዓትን እያስተካከሉ በነበረበት ዘመን መኮንን አያሌ ጀብዱዎችን ፈጸሙ፡፡
ጀግና የጦር መሪ፣ ወታደሮቻቸውን የሚወዱ፣ በወታደሮቻቸውም የሚወደዱ፣ ለሀገራቸው ታማኝ ነበሩና ምኒልክ የደጅ አዝማችነት ማዕረግ ሰጥተው ለሐረርና አውራጃው ገዥና የጦር አለቃ አድርገው ሾሟቸው፡፡ ሐረርን እና አውራጃውን በሚገባ አቀኑ፡፡ ታላቅ ነገርንም አደረጉ፡፡ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው በተቀቡ ጊዜም እኒያን በቤታቸው ያደጉ ጀግና የጦር መሪ የራስነት ማዕረግ ሰጧቸው፡፡ ራስ መኮንንም ተሰኙ፡፡ በዚህ ስማቸውም ዝናቸውም ናኘ፡፡ በሀገራቸው የዝናቸው ነገር ከዳር ዳር ተሰማላቸው፡፡ አበው ዙፋን የቀራቸው ባለ ዝና ይሏቸዋል፡፡
አስቀድሞ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በማጽናት፣ የተመቻቸ ሥርዓት በመሥራት ኀያል ነገር ያደረጉት ራስ መኮንን የውጭ ጠላት በተነሳ ጊዜም ከሚወዷቸው ንጉሥ ጋር ዘምተው ጠላትን ድባቅ መቱት፡፡
የኢጣልያና የኢትዮጵያ አለመግባባት እያየለ ሄዶ ጦር ወደ መማዘዝ ደረሰ፡፡ በቅኝ ግዛት ልክፍት የተያዘችው ኢጣልያ የኢትዮጵያን ወሰን አልፋ ገባች፡፡ ንጉሠ ነገሥት እምዬ ምኒልክም ዓዋጅ አስነግረው ጠላት ወዳለበት ገሰገሱ፡፡ የኢጣልያ ወራሪ ጦር እየወረረ መጥቶ ነበር፡፡ ወረኢሉ ላይ ከትተህ ጠብቀኝ ያሉት እምዬ ወረኢሉ ላይ ከሠራዊቱ ጋር ተገናኙ፡፡ በዚያም ምክር ከተደረገ በኋላ በራስ መኮንን የበላይ አዛዥነት ጦር ወደፊት አስቀድመው ላኩ፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው ” ምኒልክ ራስ መኮንን እና ፊታውራሪ ገበየሁን ወደፊት መንገድ ጠራጊ ሰደዱ። አምባላጌ የዚያን ጊዜ የኢጣልያ ጦር ሁለት ሺህ ያህል ሆኖ ከጥቂት መድፍ ጋር ማጅኦር ቶዜሊ በሚባል ሹም እግር ታዝዞ ተቀምጦ ነበረ። አሸንጌ ሲደርሱ ራስ መኮንን መጣሁብህ አትችለኝምና ሽሽ ከፊቴ አትቁም ብለው አምባላጌ ለነበረው ጦር አለቃ ለማጅኦር ቶዜሊ ላኩ። ይሄው ማጅኦር ቶዜሊ ግን አሻፈረኝ ከዚህ ሥፍራ አልነቃነቅም እስቲ ከደፈርክ ንካኝ ብሎ ላከ። ወዲያው ራስ መኮንን ደረሱና ከበው ይዘው አንድ ሳይቀር በሰናድር አረገፉት። ጥቂትም ቢቀር እስከ ጠመንጃውና እስከ መድፉ በራስ መኮንን እጅ ወደቀ” ብለዋል የታሪክ ጸሃፊው፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መጽሐፋቸው የአምባላጌውን ውጊያ በተመለከተ ሞልቴዶ የተባለውን ጣልያናዊ ዋቢ አድርገው ሲጽፉ” አበሾች በጥይት ተቀበሉን፡፡ በየድንጋዩ ኋላ አበሾች ተደብቀው ኖረዋል፡፡ ከበላያችን ይተኩሳሉ፡፡ ከፊታችንም ይተኩሳሉ፡፡ ከጎናችንም ይተኩሳሉ፡፡ መድረሻ አሳጡን፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሚሸሸው የእኛ ወታደር ይገፋናል፡፡ በቅሎዎች እየረጋገጡን ያልፋሉ፡፡ ይጋፋሉ፤ በግራም በቀኝም ሬሳና ቁስለኛ ብቻ ተከምሯል፡፡ የቆሰሉት ሰዎቻችን እርዱን እርዱን ይላሉ፡፡ የሚሰማቸው የለም፡፡ በየትም ቦታ በየትም አበሾች እየተከታተሉ ይተኩሱብናል፡፡ ʺ ብለዋል፡፡
ራስ መኮንን የአምባላጌን ጦር ድል ከመቱ በኋላ በአስፈሪ ግርማ ወደ መቀሌ ገሰገሱ። መጣውብህ እያሉ አስቀድመው ድል እንደሚመቱት እየተናገሩ የሚሄዱት የጦር መሪ ጠላትን ያስጨንቁት ዘንድ ተፋጠኑ። እንኳን አባ ዳኛውን ያክል ንጉሥ ሂድ ብለው ልከዋቸው፣ እንኳን እቴጌን ያክል ንግሥት እሰይ የእኔ ጀግና እያሉ አሞግሰዋቸው ለወትሮው እሳት የላሱ፣ የአንበሳ ግርማን የለበሱ ጀግና ናቸውና በቁጣና በእልህ ገሰገሱ። ወዮለት ለጠላት፣ አስፈሪው ሰው ጦራቸውን አስከትለው ገስግሰውበታልና። ኢትዮጵያ የምትመካባቸው፣ ንጉሥና ንግሥቷ የልባቸውን ሙላት የማይጠራጠሯቸው ልበ ቆራጥ ጠላትን እንዳልነበር ሊያደርጉት ነው። መቀሌ ደረሱ። አስፈሪ የተባለውን የጠላት ምሽግ ከበው ይዘው ይዋጉ ጀመር።
ንጉሡም ተጉዘው በግርማ ደረሱ፡፡ የመቀሌ ምሽግም በታላቅ ጀግንነት እና በረቀቀ ጥበብ ተለቀቀ፡፡ ጠላት ሸሸ፡፡ ኀያሉ ጦርነት ቀረበ፡፡ የኢትዮጵያ ጀግና ሠራዊት ወደ ዓድዋ ገሰገሰ፡፡ የራስ መኮንን ወዳጅ የሆነና የኢጣልያ ሰላይ የነበረው ፌልተር ራስ መኮንን በኢጣልያ በነበራቸው ጉብኝት ስላዩት የጦር መሳሪያ ብዛት እና ዘመናዊነት እያስረዳ ኢትዮጵያ ከኢጣልያ ጋር ከመዋጋት ይልቅ የኢጣልያን ጥያቄ መቀበሉ እንደሚያዋጣት ለማስፈራራት ሞክሮ ነበር፡፡ ልበ ደንዳናው ጀግና እንኳን በፎከረ በወረወረ እንደማይደናገጡ አላወቀምና፡፡ ራስ መኮንን ከሌሎች ጀግና ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው በዓድዋ ተራራ ላይ ጠላትን ከበቡት፡፡ በጥይት አረር ቆሉት።በዓድዋ ተራራ ላይ ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ አለች፡፡ ኢጣልያ ተንኮታኮተች፡፡
ጀግናው የጦር መሪ ከዓድዋ ጦርነት በኋላም ለሀገራቸው አያሌ ጀብዱዎችን ሠሩ፡፡ በታማኝነት አገለገሉ፡፡ ጊዜው ሄደ፡፡ የጠላት ጥይት ያልነካቸው፣ የጠላት ጦር ያልደፈራቸው ራስ መኮንን ታመሙ፡፡ እኒያ ጀግና አቅም አነሳቸው፤ በቁጣ በተመላለሱበት ጎዳና መራመድ አቃታቸው፣ በፈረሳቸው ላይ በግርማ መታየት ደከማቸው፡፡
ልጃቸው አጼ ኃይለ ሥላሴ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ በሚለው መጽሐፋቸው ስለ አባታቸው ሲጽፉʺ ልዑል አባቴ በ1898 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ለመውጣት በጥር 4 ቀን ከከተማቸው ከሐረር ተነሱ፡፡ በዚህም ጊዜ ጥቂት አሟቸው ነበር፡፡ በጥር ዘጠኝ ቀን ቡርቃ በሚባለው ወንዝ ሰፈር አድርገው የጥምቀትን በዓል አክብረው ከዋሉ በኋላም ሕመሙ ስለ ጸናባቸው ወደኋላ ተመልሰው ቁልቢ ከሚባለው ከሁለተኛው ከተማቸው ገብተው በሐኪም ይታከሙ ጀመር፡፡ በዚህ ጊዜ አባቴ እኔን ለማየት ናፍቀው ስላስጠሩኝ ወደ ቁልቢ ወጣሁ፡፡ አኳኋናቸውንም ለማየት ወደ ተኙበት ቤት ስገባ በአጠገባቸው ቆሜ ያዩኝ እንደሆነ ስለ በሽታቸው ጽናት በአንደበታቸው መናገር ሲያቅታቸው ባይናቸው እየጠቀሱ ተቀመጥ ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም ከአጠገባቸው አለመለየቴ ፈቃዳቸው መሆኑን ስለተረዳሁት ቀኑን ሁሉ በአጠገባቸው እየተቀመጥኩ እውል ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስልጣን የተቆረጠውን የሞት ፍርድ ሰዓት ያንድ አባትና ልጅ ፍቅር ይቅርና የብዙ ሰውም ፍቅር ቢሆን ሊያስተላልፈው አይችልምና በመጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ቁልቢ ላይ አርፈው በሐረር እርሳቸው በተከሉት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተቀበሩ” ብለዋል፡፡
እምዬ ምኒልክ ታማኛቸው አርፈውባቸዋልና አብዝተው አዘኑ፡፡ እንባቸውን አፈሰሱ፡፡ የምኒልክን ሐዘን ያዩ የሀገሬው ሰዎችም
ʺ ዋ አጼ ምኒልክ እግዚአብሔር ያጥናዎ
በየበሩ ቋሚ ከልካይ ሞተብዎ፡፡
ሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ
ማን ዋስ አገኘና ሐረርጌ ተፈታ፡፡
ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሳሳና በራ ገለጣቸው
እንግዲህ ምኒልክ ምን ራስ አላቸው፡፡”
እያሉ ተቀኙላቸው፡፡ እምዩ ምኒልክ በአዲስ አበባ ሐዘን ተቀመጡ፡፡ የጀግናውን ተዝካርም አወጡ፡፡ ስለጀግናው እረፍት የሚቀኙ ሰውም እንዲህ አሉ፡፡
” የዓድዋ ፊታውራሪ ያረርጌው ደጀን
እንደ አንድ ሰው ሞተ ራስ መኮንን” እየተባለ ተገጠመላቸው፡፡ ግርማቸው የሚያስፈራው ጀግና ከአያሌ ታሪኮች፣ ከከበሩ ጀብዱዎች በኋላ እንደ አንድ ሰው አረፍ አሉ፡፡ ስማቸውን ከመቃብር በላይ አኑረው ጋደም አሉ፡፡
ʺየሐበሻ ሁሉ ማረፊያ ነበረ
አልጋውን መኮንን ይዞት ተቀበረ።” ታላቁ ጀግና ማረፊያውን፣ መጠለያውን ይዘውት ተቀበሩ፡፡ የኢትዮጵያ መከታ ተቀበሩ፡፡ ያ ጀግና አለፉ፡፡ ዳሩ ትውልድ የማይረሳው፣ ዘመን የሚያወሳው ታሪክ ጽፈዋልና በልብ ውስጥ ይኖራሉ፤ ጀግናው የጦር መሪ ሆይ ክብር ይገባዎታል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!