
ባሕር ዳር:መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማሪታይም አካዳሚ ለ20 ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 39 ተማሪዎች አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፍሬው ተገኝ (ዶ.ር) ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እየተሠጠ ያለው የመርከበኞች ስልጠና ኢትዮጵያ የተማረ የሰው ኀይል ለውጭ እንድታቀርብ አስችሏታል ብለዋል። ኢትዮጵያ የባሕር ወደብ ባይኖራትም ዜጎቿ በሌሎች ሀገሮች የበለጠ ተመራጭ ኾነው እንዲመረጡ እያደረገ ነው ብለዋል። የሌሎች ሀገሮችን የተሳሳተ አመለካከትም እንዲያስተካክሉ ያደርገዋል ብለዋል።
“እናንተ ተመራቂዎች ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳድራችሁ ስልጠናውን በብቃት አጠናቃችሁ ለዚህ ቀን በመድረሳችህ ዕድለኞች ናችሁ ብለዋል።
ዶክተር ፍሬው እንዳሉት እስካሁን ከተመረቁ ተማሪዎች 2ሺህ ተመራቂዎች በዓለም ላይ ተቀጥረው እየሠሩ ነው። ከሚከፈላቸው ደመወዝ 80 በመቶ በውጭ ሀገር ገንዘብ ይቀመጥላቸዋል። ይህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ በኩል ድርሻው ጉልህ ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ሌሎች ሀገር አቀፍ ሥልጠናዎችንም እየሠጠ ነው ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አርዓያ እየኾነ ነው ብለዋል።
ማሪታይም(የመርከበኞች) ሥልጠና የሚሰለጥኑ ተማሪዎች በመካኒካል ኢንጅነሪንግ ዲግሪያቸውን አጠናቀው በውድድር በመኾኑ ሁሉም በዚህ ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎች ማሪታይምን ምርጫቸው እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የማሪታይም አካዳሚ ኮማንዳንት ቻርል ኮቴዝ በበኩላቸው ውጣውረዱን አልፋችሁ ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ትምህርት በዚህ የሚያበቃ ሳይኾን የበለጠ በመማር ለራሳችሁም ኾነ ለሀገራችሁ ድርሻችሁን እንድትወጡ ሲሉ መልዕክት አስተላለፈዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል አላዛር ሙሉጌታ በስልጠናው የተሻለ እውቀት ማግኘቱን እና ቀጣይ ለመማር ማቀዱን ነግሮናል። በነበረው የስልጠና ጊዜም ኢትዮጵያን እንዲያውቃት አድርጎታል። ትምህትቱ ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ጋር ያጣመረ በመኾኑ ለቀጣይ ሥራችን ችግር አይገጥመንም ብሏል። ሌላው ተመራቂ አበበ ትንሳኤ እንዳለው በሥልጠናው በቂ እውቀት እንዳገኘ ነግሮናል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!