
ባሕር ዳር:መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን የግል ባለኃብቱ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
በአምራች ዘርፉ የተሰማሩ ከ350 በላይ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ትናንት ምሽት በተዘጋጀ መርኃ ግብር ይፋ ተደርጓል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አቶ ዓለሙ ስሜ፣ባለኃብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኤክስፖው ዋነኛ ዓላማው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተመረቱ ምርቶች፣የተገኙ ውጤቶችን በሀገር፣አህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ መሆኑም ነው የተገለጸው።
የአምራቾችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር፣ልምድ እንዲለዋወጡ ማስቻል እና የገበያ ዕድሎችን መፍጠርም እንዲሁ።
በኤክስፖው ላይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ በአምራች ዘርፉ የሚሳተፉ 350 ድርጅቶች ምርቶታቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ ታውቋል።
300 ሺህ የሚጠጉ ጎብኚዎች በኤክስፖው ላይ እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የፋይናንስ ተቋማት፣የንግድ ማኀበራት፣ላኪዎች እና ባለኃብቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ በዚሁ ጊዜ ፤በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ንቅናቄው ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት እና የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ንቅናቄው በቀጣይነት ይበልጥ እንዲጠናከር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስኬታማ እንዲሆን የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች እና የከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህም ከመሬት አቅርቦት፣ከመሰረተ ልማት አኳያ የሚገጥሙ ችግሮች እንዲፈቱ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፣ በቀጣዩ ወር የሚካሄደው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ እንደ ሀገር በአምራች ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
አምራቾችና ባለኃብቶች በኤክስፖው በመሳተፍ ዕድሉን በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዕለቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መለያ /ሎጎ/ ይፋ ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!