ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ስኬታማነት ብሪታንያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች።

47
ባሕር ዳር:መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የብሪታኒያ የልማት እና አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪው ሚሸልን በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ በልማት ትብብር ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ደመቀ፥ ይህ ግንኙነት መጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በወቅታዊነትም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ በማድረግ ረገድ ተግራዊ እየሆኑ ስላሉ እርምጃዎች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፥ የስምምነቱ የእስካሁን ሂደት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል።
በግጭቱ ወንጀል በመፈፀም የሚጠረጠሩ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግም የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቶ ደመቀ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህ ተግባር በአሁኑ ወቅት በጦርነት እና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በብሪታኒያ የልማትና የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አንድሪው ሚሸል በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በመንግስት በኩል የተወሰደውን እርምጃ እና የታየውን ቁርጠኝነት ሀገራቸው እንደምታደንቅ ገልጸዋል።
ለስኬታማነቱም ሀገራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ነው ያረጋገጡት።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ከድርቅና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ያጋጠማትን ፈተና ብሪታኒያ እንደምትገነዘብ በመጠቆም ለዚህ የሚሆን ድጋፍ ከረድኤት ድርጅቶችና ከሌሎች ዓለማቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ በሁለትዮሽ እና በሌሎች የትብብር መስኮችም ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ትምህርቴን ስላጠናቀቅኩ ዲግሪዬን በፖስታ ላኩልኝ እኔን ግን የሀገሬ ገበሬዎች ይፈልጉኛል” ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር
Next article“የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን የግል ባለኃብቱ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል