
ባሕር ዳር:መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መደበኛ ትምህርታቸውን ከአራተኛ ክፍል ላይ ጀምረው፣ ሁለተኛ ዲግሪን ዘለው የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በላቀ ውጤት ያጠናቀቁ ዕንቁ ምሁር ነበሩ፡፡ ይህ ሰው ወደ ዌልስ ዩኬ አቅንተው የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን 9 ወራትን ቀድመው አጠናቀው “ዲግሪዬን በፖስታ ላኩልኝ እኔን ግን የሀገሬ ገበሬዎች ይፈልጉኛል” ብለው የአውሮፓን ቅንጡ ሕይዎት ንቀው የመጡ የወገን ጠበቃ ናቸው፡፡
እኝህ ሰው በምዕራባዊያኑ የሥነ-ምህዳር ጠበብት ዘንድ “ቻምፒዮን ኦፍ ዘ ኧርዝ” የሚል መጠሪያ የተቸራቸው ድንቅ ሎሬት ነበሩ፡፡ ከ50 በላይ ኢትዮጵያዊያንን ከከፋ ሕይዎት አውጥተው እና አስተምረው ለተሻለ ሕይዎት ያበቁ የተፈጥሮ ብቻ ሳይኾን የፍጡራን አለኝታም ነበሩ፡፡ በሥነ-ምህዳር ሳይንስ አያሌ ምሁራንን ተክተው ያለፉ የሕይዎት ዘመን አስተማሪም ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉን የሥነ ምህዳር ምሁራን አሳምነው፤ የምርጥ ዘር ባለመብት ነን ባይ ካምፓኒዎችን እና የምርምር ተቋማትን ሞግተው በዓለም ላይ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን የዘር መብት ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡ የምድራችን ጀግና እና ባለውለታ ናቸው፡፡
እኝህ ሰው “ሦስተኛው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ” የሚል መጠሪያ የተቸራቸው ደራሲ፣ ጋዜጠኛ፣ አስተማሪ እና የሐሳብ ሰው የነበሩት ጋሽ ስብሃትለአብ ገብረ እግዚአብሔር ታናሽ ወንድም ናቸው፡፡ የዚህን የሥነ ምህዳር ጀግና የሕይዎት ጉዞ በአጭሩ እንዲያስቃኙን ከደራሲ እና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ጋር አጭር የሥልክ ቆይታ አድርገናል።
እርሳቸው እንዳሉን ተፈጥሮ ጠበቃዋን ተነጥቃለች፤ ምድር ባለውለታዋን አጥታለች፡፡ ዓለም ላይ ለቆዩባቸው ዓመታት ለተፈጥሮ ተገቢውን ውለታ ከከፈሉ እና በጣት ከሚቆጠሩ ብድር መላሾች መካከል በእርግጠኝነት ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር አንዱ ናቸው ብለዋል፡፡
ምዕራባዊያኑ “ቻምፒዮን ኦፍ ዘ ኧርዝ” ሲሉ ያሞካሿቸውን የሥነ-ምህዳር ምሁር ኢትዮጵያዊያኑ ጸሐፍት ደግሞ “የምድራችን ጀግና” ሲሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ብዙዎች በሀገራቸው ኢትዮጵያ “መሬት ላራሹ” ብለው ለትግል ተነስተው አራሹን ገበሬ የመሬት ባለቤት ማድረግ ችለዋል፡፡ ነገር ግን ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ብቻቸውን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ለሚኾኑ የዓለማችን አርሶ አደሮች “ተፈጥሯዊ የዘር ባለቤትነት መብታቸውን አስከብረው” በቀላሉ የማይከፈል ውለታ ጥለውላቸው አልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው የሥነ-ምህዳር ሳይንስ ጠበብት አደጋ ለተጋረጠባት ተፈጥሮ ደብዛዋ ፈጽሞ እንዳይጠፋ ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ሰርተዋል፡፡
1932 ዓ.ም ይህችን ምድር የተቀላቀሉት ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ትውልዳቸው በትግራይ ክልል ከዓድዋ ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ በምትገኝ እርባ ገረድ በተባለች ስፍራ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር መሰረታዊውን የሂሳብ ትምህርት ዕውቀት እና ከአማርኛ እስከ ግዕዝ፤ ከትግርኛ እስከ እንግሊዝኛ ልሳነ ብዙ ቋንቋን በቤታቸው ውስጥ በታላቅ ወንድማቸው እገዛ እየተማሩ ነው ያደጉት ያሉን ዕውቁ ጸሃፊ እና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ መደበኛ ትምህርታቸውን የጀመሩት ደግሞ ከ4ኛ ክፍል ላይ እንደነበርም አጫውተውናል፡፡
1948 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተናቸውን ወስደው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት የያኔው ብላቴና የኋላኛው ዘመን የምድራችን ጀግና 1949 ዓ.ም ላይ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ጀኔራል ዊንጌትን ተቀላቀሉ፡፡ የጀኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ቆይታቸው ስኬታማ እንደነበር የሚነገርላቸው ዶክተር ተወልደ ብርሃን የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስደው እጅግ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት ጉዟቸውን አንድ ሲሉ ጀመሩ፡፡
በሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የሕይዎት ጉዞ ዙሪያ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ያሳተሙት እና የቅርብ ሰው የኾኑት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ለአራት ዓመታት የዘለቀው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቤት ቆይታቸው የላቀ ስኬት የተመዘገበበት እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በከፍተኛ ውጤት የተመረቁት የምድራችን ጀግና ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ ነበሩም ብለውናል፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ስኬታማ የትምህርት ቤት ቆይታ በኋላ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ ዌልስ ዩኬ ያቀኑት ወጣቱ ተወልደ ብርሃን የገቡበት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክስ አባላት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውጤታቸውን አይተው ማስተር ወይም ሁለተኛ ዲግሪ መማር ሳያስፈልግህ የዶክትሬት ዲግሪህን መቀጠል ትችላለህ ብለው በመወሰናቸው የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡
ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዘነበ ወላ ፤ የምድራችን ጀግና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ገና የ9 ወራት የቆይታ ጊዜ እየቀራቸው አጠናቀቁ ይሉናል፡፡ ነገር ግን ሰውየው “ያስተማሩኝ ወገኖቸ ድሃ ገበሬዎች ናቸው፤ የተማርኩት ከድህነታቸው ላይ እየተቆረሰ በተከፈለ ግብር ነው፤ 9 ወራትን በዚህ መቆየት አልችልም፤ በተማርኩት ልክ ሄጀ ወገኖቸን ማገልገል ይኖርብኛልና ወረቀቴን በፖስታ ላኩት ብለው ወደ ሀገራቸው ቀድመው ተመለሱ” የሚሉን ጉምቱው ጸሃፊና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ዌልሳዊያንም ቃላቸውን ጠብቀው የዶክተር ተወልደ ብርሃንን የትምህርት ማስረጃ በፖስታ ላኩላቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በርካታ ምሁራንን ያፈሩት ሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እንዲቋቋም የጎላ ድርሻ ነበራቸው፡፡ ከሪዮ ዲጀኔሪዮ እስከ ኮፐን ሀገን የሥነ ምህዳር ጠበቃ በመኾን የዓለማችን መሪዎች ስለተፈጥሮ የተዛባውን ዕይታቸውን እንዲያርሙ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምክረ ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡
የዘረ መል ምህንድስና ከተፈጥሮ ሀብት ጋር እንዳይቀላቀል በብዙው ታግለዋል፡፡ ከምንም በላይ አስመራ ዩኒቨርሲቲን በመሩበት ዘመን በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት አንድም ተማሪ ሳይጎዳ ወደ አዲስ አበባ እንዲደርሱ ኅላፊነቱን ወስደው የሰሩ መምህር ብቻ ሳይኾኑ አባትም ናቸው ይሉናል፡፡ ይህንን ሁሉ ጥረታቸውን ከግምት ውስጥ አስገብተው 1993 ዓ.ም የኢግራም ኖቬል ሽልማት ፣የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 1998 ዓ.ም “ቻምፒዮን ኦፍ ዘ ኧርዝ” ሲል ሸልሟቸዋል፡፡ 1999 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት፣ 2000 ዓ.ም ዘ ጋርዲያን 50 የምድራችን ደህንነት ያስጠበቁ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው ሲል ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡
ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር በሥነ ሕይወትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከ30 በላይ ጥናቶችን በማሳተም፣ በዚሁ ዙሪያ በርካታ መጽሃፍትን በመጻፍ፣ የአካባቢ ጥበቃ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅሙ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ በነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በተካሄደው 4ኛው የበጎ ሰው ሽልማት ደግሞ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በብቃት በመወጣት ዘርፍ አሸናፊ ኾነዋል፡፡
“ሞት ተፈጥሯዊ የሕይወት ሕግ ነው” የሚሉት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ የምድራችን ጀግና 83 ዓመታት ከአንድ ወር በምድር ላይ ቆይተው መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም የምድራችን ጀግና ከምድራዊ ድካማቸው አረፉ ይሉናል፡፡ እኛም የገነት በሮች ይከፈቱለዎት ስንል ሸኘናቸው፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!