በመስኖ ከለማው ስንዴ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

92
ደሴ :መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ አሥተዳደር ዞን በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮች በአካባቢው ተዘርቶ የማያውቀውን የስንዴ ዘርን ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከሩት ባሳለፍነው 2014 ዓ.ም ላይ ነው።
በርካታ አርሶ አደሮች በአካባቢው ተሞክሮ የማያውቀውን የስንዴ ዘር ጥቂት አርሶ አደሮች ዘርተው ውጤታማ እንደኾኑ በማየታቸው የአካባቢው አብዛኛው አርሶ አደር አሁን ላይ በመስኖ ስንዴን እያመረቱ እንደሚገኙ አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመቀራረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየጣሩ እንደሚገኙ የገለጹት አርሶ አደሮቹ በቀጣይ ዘመኑን የዋጁ የእርሻ መሳሪያዎች እንዲቀርቡላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም እንድሪስ በ2014 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴ ተዘርቶ 37 ኩንታል ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ ማግኘት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም በዘር ከተሸፈነው የስንዴ ማሣ ላይ ከ17 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት።
በዘንድሮው ዓመት በአንደኛ ዙር 310 ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ዘር ለመሸፈን ታቅዶ 435 ሄክታር መሬት መሸፈኑን ኀላፊው ተናግረዋል።
ዘመናዊ ትራክተሮችንም ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየተሠራ እንደሚገኝና በቅርቡ ለአርሶ አደሩ እደሚያስረክቡ አቶ አደም አስረድተዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleʺመገፋት የበዛባቸው፣ የሞቀ ቤት የናፈቃቸው”
Next article“ትምህርቴን ስላጠናቀቅኩ ዲግሪዬን በፖስታ ላኩልኝ እኔን ግን የሀገሬ ገበሬዎች ይፈልጉኛል” ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር