ʺመገፋት የበዛባቸው፣ የሞቀ ቤት የናፈቃቸው”

89

ባሕር ዳር: መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መገፋት በዝቶባቸዋል፣ መሳደድ ሰልችቷቸዋል፣ የሞቀ ቤት፣ ሰላም የሆነ ቀዬ ናፍቋቸዋል፡፡ በሚወዷት ሀገራቸው፣ በሚሳሱላት ቤታቸው መኖር ርቆባቸዋል፡፡ በሞቀ ቤታቸው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት፣ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፉት ደጋጎች ከሰው ፊት መቆም አሳዝኗቸዋል፡፡ አርሰው የሚበሉት፣ ከማሳቸው ተፈናቅለዋል፣ የተራበን የሚያጎርሱት የሚጎርሱት ተቸግረዋል፤ የተጠማን የሚያጠጡት ተጠምተዋል፤ ባለቤቶቹ ቤት አልባ ሆነዋል፡፡
ሞተው ባጸኗት፣ ደም አፍስሰው፣ አጥንት ከስክሰው ባቆሟት፣ ከነብሳቸው አስበልጠው በሚወዷት፣ በሚመኩባት፣ በሚያከብሯት፣ ለዘመናት በተዋደቁላት፣ አንድነቷን ባጸኑላት፣ ጠላቶቿን በደመሰሱላት ሀገራቸው በሰላም መኖርን ናፍቀዋል፤ እርስታቸውም፣ እትብታቸውም በኢትዮጵያ የሆነው ደግነትን፣ ጀግንነትን፣ አንድነትን እና የከበረ ኢትዮጵያዊነትን በአንድ አዋህደው የያዙት፣ ከራስ በላይ ሌላውን የሚወዱት፣ ስሞት አፈር ስሆን እያሉ የሚመግቡት ደጋጎች ቤት አጥተዋል፣ የሰው እጅ እያዩ ለመኖር ተገደዋል፡፡
ረሃብና ጥማቸው በሰዎች ያልታየላቸው፣ ፍትሕ አዋቂ ሳሉ ፍትሕ ፊቷን ያዞረችባቸው፣ በደልና መከራቸው የተደበቀባቸው፣ ውለታቸው የተረሳባቸው፣ ወርቅ እየሰጡ ጠጠር የሚመለስላቸው ደጋጎች ሰላምን ይሻሉ፣ በቤት መኖርን ያልማሉ፣ ስደታቸው እና እንግልታቸውን ዓይኖች አላዩላቸውም፣ ጀሮዎች አልሰሙላቸውም፤ በልባቸው ርህራሄ አላሳዩዋቸውም፡፡
ለነጻነት የዘመቱት፣ ለክብር የሞቱት፣ ፈትፍተው የሚያጎርሱት፣ አውልቀው የሚያለብሱት፣ ከአልጋ ወርደው እንግዳ የሚያስተኙት፣ ሀገርና ሕዝብ የሚያከብሩት፣ ሠንደቅ የሚያፈቅሩት፣ ለበደል እጃቸውን የማያነሱት፣ ለመስጠት የማይሳሱት፣ ውለታ የማይረሱት፣ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩት፣ ሕግና ሥርዓት የሚያከብሩት፣ ለፍትሕ የሚከራከሩት፣ ስለ እውነት፣ በእውነት የእውነት የሚኖሩት መገፋቱ በዝቶባቸዋል፡፡ መሳደድ በርክቶባቸዋል፡፡ ለበረከት የሚተጉት፣ ለስጦታ እጃቸውን የሚዘረጉት፣ ታማኝ፣ ኩሩ እና ቅን የሆኑት ዛሬ ላይ ከሰው ፊት ወድቀዋል፣ ጊዜ ገፍቷቸው እጃቸውን ለመስጠት ሳይሆን ለመቀበል ዘርግተዋል፡፡
ከኢትዮጵያዊነት ማማ ላይ የማይወርዱት፣ ከከፍታው ዝቅ የማይሉት ደጋጎቹ በማንነታቸው ተፈናቅለው፣ የሌለባቸውን እዳ ተቀብለው፣ በመጠለያ ጣብያ ለመኖር ተገደዋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መገፋት የበዛባቸው፣ መከራ ጀርባቸውን ያጎበጠባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ይገኛሉ፡፡ በዞኑ ከቀያቸው ርቀው ለዓመታት በችግር ውስጥ የሚያሳልፉ አሉ፤ አዳዲስ በደል ቀማሾችም ከተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው የፈተናውን ሕይወት ይቀላቀላሉ፡፡ ንጹሐን ወገኖች ከተደላደለ ሕይወታቸው ወጥተው የመከራ ሕይወትን ይገፋሉ፡፡ ሀሩር እና ውርጩ፣ ረሃብና ጥሙ ይፈራረቅባቸዋል፡፡
ቤትዬ ደርቤ ከአሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በ2013 ዓ.ም ነበር ወደ ደብረብሃን የመጡት፡፡ በሆቴል ሥራ፣ በንግድና በእርሻ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩት ሁለገቡ ቤትዬ አሁን ላይ የሰው እጅ እያዩ ከሚያድሩት ጎራ ተቀላቅለዋል፡፡ ሃብትና ንብረት ካፈሩበት፣ ተወልደው አድገው ብዙ ካሳለፉበት ቤታቸው ባዶ እጃቸውን እንደወጡ ነግረውኛል፡፡ እቃ ጭነው መውጣት አለመቻላቸውን የተናገሩት ቤትዬ ህይወታቸውን ለማትረፍ የከበዱ ፈተናዎች አልፈው ደብረ ብርሃን መድረሳቸውንም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ በመጠለያ ተጠልለው እንደሚኖሩም ነግረውኛል፡፡ ʺ በመጠለያው ውስጥ ጧሪ የሌላቸው አዛውንት፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትና አካል ጉዳተኞች ይኖራሉ” ነው ያሉኝ፡፡ ከመንግሥት እየተደረገ ያለው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ረሃብ እያጠቃቸው መሆናቸውንም ነግረውኛል፡፡ ሕይወት በመጠለያ ውስጥ ፈታኝ እንደሆነችባቸውም ገልጸዋል፡፡
ʺበመጠለያ ውስጥ ያሉ ወገኖችን ያቆዬው የደብረ ብርሃን ሕዝብ ነው፤ እንጀራና ወጥ እያዋጣ ሲደግፍ ቆይቷል፤ አሁን ድረስ ይደግፋል፤ እኛ ሃሳባችን እና ሕልማችን ወደ ቦታችን ተመልሰን እንኖራለን ነበር፤ እንኳንስ ወደ ቤታችን ልንመለስ በየጊዜው የሚፈናቀለው ቁጥሩ እየጨመረ ከመሄድ ውጭ ሌላ መፍትሔ የለም፡፡ የእኛ ዘላቂ ሁኔታ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ እኛ መንግሥትን የምንደግፍ እንጂ መንግሥትን የምንጋፋ አይደለንም፤ ንፁሐን ገበሬዎችና ነጋዴዎች ነን፤ በመኾኑም መንግሥት ሊደግፈን ይገባል” ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ምግብና መጠለያ ያስፈልገናል የሚሉት ቤትዬ አርሰን እና ነግደን የምንኖር ሰዎች እስከመቼ ድረስ ነው በእርዳታ የምንኖረው ? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እንደሚሹም ገልጸዋል፡፡ ሕፃናት እንደ እኩያቸው እየተማሩ አይደለም ብለዋል፡፡ መንግሥትና ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ካልደረሱልን አደጋ ውስጥ ነን ነው ያሉት፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ ከአንድ ዓመት በላይ በመጠለያ ውስጥ የቆዩት አልማዝ ድንቁ በመጠለያ ውስጥ መኖር ከብዶናል ብለዋል፡፡ ʺብዙ ሰቆቃ አለ፣ ወደ ቦታችን እንግባ ብንልም አልሆነም፣ ግራ ገብቶናል” ብለውኛል፡፡ ቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበርም ነግረውኛል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አበባው መሠለ በዞኑ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፤ በዞኑ ለዓመታት ከቆዩት ተፈናቃዮች በተጨማሪ በየቀኑ አዳዲስ ተፈናቃይ ወገኖች እንደሚመጡም ተናግረዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በመጠለያዎች ተጠልለው እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ ንጹሃን ወገኖች ችግር ውስጥ ናቸውም ብለዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ወደ አካባቢው ሊገቡ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ ብቻ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ለወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡ በክልሎች የሚስታዋሉ ችግሮችን በመፍታት የወገኖችን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡ ከአቅማችን በላይ ሆኗል ብለን ለሚመለከተው አካል አቅርበናልም ነው ያሉት፡፡
ንፁሐን፣ ሕፃናት እና አረጋውያን በችግር ውስጥ ናቸው፣ አሁንም ተጨማሪ ወገኖች እየተፈናቀሉ እየመጡ ነው፤ ይህም ችግሩን አባብሶታል ነው ያሉት፡፡ ዜጎችን በረሃብ ከመሞት ለመታደግ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ወገኖችን ወደ ቀያቸው መመለስ ይገባዋልም ነው ያሉት፡፡
የፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ታየ ጌታቸው ደብረ ብርሃን ለሚገኙ ወገኖች መንግሥትና ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ለተፈናቃዮች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ይሁን እንጅ በመጠለያ ውስጥ ያሉ ወገኖች በበኩላቸው በቂ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልሆነና ችግር ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤትም የነዋሪዎችን ሀሳብ በመጋራት አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘበው።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሕዝባዊ አቤቱታ መቀበያ መድረክ በባሕርዳር ከተማ ሊያካሂድ መኾኑን ገለጸ።
Next articleበመስኖ ከለማው ስንዴ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።