የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሕዝባዊ አቤቱታ መቀበያ መድረክ በባሕርዳር ከተማ ሊያካሂድ መኾኑን ገለጸ።

81
ባሕር ዳር :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጭ እና በዘፈቀደ ተነፍገናል የሚሉ ሰዎችን አቤቱታ መቀበያ መድረክ በባሕርዳር ከተማ ሊያካሂድ መኾኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል። ጉዳዩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኮሚሽኑ የሴቶችና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በሁሉም አካባቢዎች የሚካሄድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ብሄራዊ ምርመራ ተጀምሯል ብለዋል። በባሕርዳር የሚካሄደው የአቤቱታ መቀበያ መድረክም የብሔራዊ ምርመራው አንዱ አካል እንደኾነ ተናግረዋል።
ይህ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ ከመጋቢት 19 – 21/2015 ዓ.ም ይካሄዳል። መብታችንን ከሕግ አግባብ ውጭ ወይም በዘፈቀደ ተነፍገናል የሚሉ ሰዎች የደረሰባቸውን በደል ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና ለሕዝብ ማካፈል እንዲችሉ የተዘጋጀ ነው ተብሏል። ይህ መድረክ በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ መሰል እና ውስብስብ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል። የመብት ጥሰቶች ተፈጽመው ሲገኙም ተጎጅዎችን የሚክስ እና አጥፊዎችን ተጠያቂ የሚያደረጉበት ጠንካራ ሕግ፣ ተቋም እና አሠራር እንዲኖር ለማድረግ ኮሚሽኑ ጥረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የሚካሄደው ሕዝባዊ የአቤቱታ መቀበያ መድረክ የሚመራው በመርማሪ ኮሚሽነሮች፣በከፍተኛ ባለሙያዎች እና በአማካሪዎች ነው። አቤቱታቸውን ያቀረቡ ተጎጅዎች መልሶ ማጥቃት እንዳይፈጸምባቸው የመከታተያ አሠራር እንደሚመቻችም ተነግሯል።
ይሕ የሕዝብ አቤቱታ መቀበያ መድረክ ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር እና ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወሰዱባቸው ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል። በመኾኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠይቋል።
ይህ አይነት የሕዝብ አቤቱታ የመቀበል ዘዴ ስለሰብአዊ መብቶች እና ተጠያቂነት በማስተማር ረገድ ውጤታማ ዘዴ እንደኾነ በመግለጫው ተጠቁሟል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
Previous articleበኩር ጋዜጣ መጋቢት 11/2015ዓ.ም ዕትም
Next articleʺመገፋት የበዛባቸው፣ የሞቀ ቤት የናፈቃቸው”