
ሁመራ :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሰሊጥ ፣ ጥጥ ፣ ማሽላና ማሾ በስፋት ከሚመረቱ ምርቶች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ ። በዞኑ በ2014/2015 የምርት ዘመን ከ4 መቶ 40 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል፡፡ ከዚህም ከ6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በላይ ተሰብስቧል።
በባለፈው ዓመት የጥጥ ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ መሸጣቸውን የነገሩን አቶ ብርሃኔ በዓታ በአንድ እጃችን መሣሪያ ይዘን የሀገርን አንድነት እያስከበርን በሌላኛው ክንዳችን መሬታችን አለስልሰን ያመረትነው ምርት የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያት ለኪሳራ እየዳረገን ነው ብለዋል።
የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዳይኾኑ ገበያ በማጣት በዝቅተኛ ዋጋ እንዲሸጥ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ባለ ሀብቱ መንግሥት የገበያ ትስስር እንዲፈጥርም ጠይቀዋል።
የአካባቢው ሙቀት ከፍተኛ በመኾኑ ባመረትነው የጥጥ ምርት ላይ የእሳት አደጋ እየፈጠረ ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረግን ነው ያሉን ሌላኛው ባለሀብት አቶ ሙላት አበበ ከሰሞኑ ከ2 ሺህ 500 በላይ ኩንታል የሚኾን የጥጥ ምርት በእሳት አደጋ መውደሙን አስታውሰዋል።
ባለፈው ዓመት አንድ ኩንታል የጥጥ ምርት በአምስት ሺህ ብር መሸጡን ያስታወሱት አቶ ሙላት በዘንድሮው የምርት ዘመን ከፍተኛ ወጭ ቢያወጡም አንድ ኩንታል ጥጥ በ2 ሺህ 500 ብር ለመሸጥ መቸገራቸውን ተናግረዋል። የገበያው ችግር መፍትሄ ካላገኘ በቀጣይ መሬታቸውን ጥጥን ጨምሮ በሌሎች ሰብሎች ለመሸፈን እንደሚቸገሩም አንስተዋል። መንግሥት የአካባቢውን አርሶ አደሮች ችግር ተመልክቶ የገበያ ትስስር እንዲፈጥር ጠይቀዋል።
በዞኑ 47 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ምርት መሸፈኑንና ከዚህም 470 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ አወቀ መብራቱ ገልጸዋል።
ዞኑ በዘንድሮው የምርት ዘመን መጠነ ሰፊ ሥራ አከናውኖ ከ6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በላይ መሰብሰብ ቢችልም በጥጥ ፣ በማሾና አኩሪ አተር ምርት ላይ በተፈጠረው የገበያ ትስስር ችግር አርሶ አደሮችና ባለ ሀብቶች ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ እየታየ ያለውን የገበያ ችግር ለመቅረፍ እንቅስቃሴ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አቶ ፍስሃ ሀጎስ ናቸው ።
በተደረገው እንቅስቃሴም የአኩሪ አተር ምርት መሸጥ መቻሉን አንስተዋል።አሁን ላይ በጥጥ ምርት ላይ እየታየ ያለውን የገበያ ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው የክልል እና የፌደራል መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!