“ጠንካራ የፓርቲ ቁመና በመፍጠር እና መንግሥት በመገንባት የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ እየተሰራ ነው ” አቶ አደም ፋራህ

73
ባሕር ዳር :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ጠንካራ የፓርቲ ቁመና በመፍጠርና ጠንካራ መንግሥት በመገንባት የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና አመራሮች ስብሰባ በፓርቲው ዋና ፅኅፈት ቤት እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አደም ፋራህ ብልጽግና ፓርቲ ባስመዘገባቸው ስኬቶች፣ ባጋጠሙ ፈተናዎች እና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎቹ ላይ በመምከር በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ውይይቱን ማካሄድ እንዳስፈለገ ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን እየተስተዋሉ ካሉ ፈተናዎች ውስጥ አንዱ በተለያዩ የፖለቲካ ተዋንያን በኩል የሚታየው በ”ነጻነት አጠቃቀም” እና በ”ነጻነት አስተዳደር” መካከል ሚዛን ያለመጠበቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሁኔታውን ለማረም የፖለቲካ አመራሩ ድርሻ ጉልኅ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡
በኢትዮጵያ “የግለሰብ” እና “የቡድን” መብቶች የተፈቀዱና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ ያላቸው ቢሆኑም በአተገባበር በኩል ችግሮች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡
በነፃነት ልምምድ ሥም የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽሩና የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎች እንዳይፈጠሩ መከላከል የአመራሩ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል፡፡
ስብሰባው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን አመራሮቹ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሠነድ ላይ ውይይት ያካሂዳሉ፡፡
በሠነዱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጻ ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የኅብረ ብሔራዊ እና ሀገራዊ ፓርቲ ምሥረታ ፣ አጣብቂኝ ላይ የወደቀውን ሀገራዊ ኢኮኖሚ በመታደግ ልማትና ዕድገትን ማስቀጠል፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት ማስከበር በሚሉት ዐበይት ጉዳዮች እና በሌሎች መስኮች የተመዘገቡ ድሎችን አብራርተዋል፡፡
በዚህ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በአመራሩና አባላት ውስጥ የአመለካከትና የተግባር አንድነት የሚያጎለብቱ ፣ ሕዝቦችን የሚያቀራርቡና ትሥሥርን የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
Next articleየጥጥ ምርት የገበያ ትስስር ባለመኖሩ ለኪሳራ መዳረጋቸውን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚገኙ ባለሀብቶች ገለጹ።