‹‹የዩኒቨርሲቲው አሠራር እንዳንሸጋገር አድርጎናል፤ ሳንሸጋገርም ሥራውን እንድንለቅ መመሪያ መተላለፉ ተገቢ አይደለም›› ሲሉ በማኅበር ተደራጅተው የሚሠሩ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

110

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ‹‹የተቀመጠው አሠራር ተገቢ በመሆኑ ሥራውን ለሌሎች ሥራ ፈላጊ ወጣቶች መልቀቅ ይኖርባቸዋል›› ብሏል፡፡

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) ተቋማት ለማኅበረሰብ ከሚፈጥሯቸው መልካም ነገሮች መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ከተመሠረተ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲም በግንባታ ሥራ፣ በግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት፣ በጽዳትና ውበት እንዲሁም በተለያዩ የውስጥ ሥራዎች ከ300 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ከስደት ተመልሰው ከመንግሥት ‹ሸድ› በመረከብ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ ብዙዎቹ በንግድ ሥራ ተሰማርተው ራሳቸውን እየቀየሩ ነው፡፡ በማኅበር ተደራጅተው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እየሠሩ ያሉ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡

የወጥ ቤት ማኅበር ሊቀ መንበሩ ዲያቆን ግርማይ ተረፈ እንደተናረው ከዚህ ቀደም ሥራ ፍለጋ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚሄዱ ወጣቶች የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተደራጅተው ሥራ ከጀመሩ ሦስት ዓመት የሞላቸው ማኅበራት እንዲለቅቁና አዳዲስ ማኅበራት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መታሰቡ ተስፋቸውን እንዳለመው ተናግሯል፡፡ ዲያቆን ግርማይ እንደሚለው ዩኒቨርሲቲው ከወጣቶች ማኅበር ጋር ቅጥር የፈጸመው በጊዜያዊነት ነው፤ ስምምነቱንም ያደረጉት በአትራፊነት ሳይሆን በወር ደመወዝ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዕለት ተዕለት ኑሯቸው አልፈው እራሳቸውን እንዲያሻሽሉ አላደረጋቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት በሦስት ዓመት ቆይታቸው ለውጥ አለማምጣታቸውን ነው ባልደረቦቹን ወክሎ፡፡

“የኮንትራት ቅጥር ለአትራፊ ማኅበር ሊሰጥ ሲገባው ቋሚ ደመወዝ እየተከፈለ በጊዜያዊነት መፈጸሙ ተገቢ አይደለም፡፡ ሲቪል ሰርቪስ የሚጠይቀውን መስፈርት ሁሉ እናሟላለን” ያለው ዲያቆን ግርማ ቅጥራቸው ወደ ቋሚነት እንዲቀየርላቸው ካልሆነም ደግሞ ማኅበሩ አትራፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው እንዲያመቻችላቸው ጠይቋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይኼነው ምሥራቅ ደግሞ ወጣቶች ተደራጅተው ሥራ ሲጀምሩ ውል መያዛቸውንና ውሉ የሚታደስበት አግባብ እንዳለም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹በቴክኒክ እና ሙያ አሠራር መሠረት የተደራጁ ወጣቶች ሽግግር አድርገው ለአዳዲስ ማኅበራት እንዲለቅቁ ይፈለጋል›› ብለዋል፡፡ “ዩኒቨርሲቲው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ዕድሉ የተሰጣቸው ወጣቶች ራሳቸውን ሊለውጡ የሚችሉበት ጊዜ እና ሁኔታ በቂ በመሆኑ ዕድሉን ያላገኙ ወጣቶች ዕድሉን ተጠቅመው ራሳቸውን እንዲለውጡበት በማሰብ እንደሆነ መረዳት አለባቸው›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን አቶ ይሄነው ይህንን ይበሉ እንጂ ወጣቶች የሚከፈላቸው ወርኃዊ ደመወዝ ከዕለት ጉርሳቸው አልፎ ሊለውጣቸው አለመቻሉን ዲያቆን ግርማይ ነግሮናል፡፡

የደባርቅ ወረዳ ቴክኒክ ሙያና ኢንተፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የወጣቶች ጥያቄ ትክክል መሆኑን አመልክቷል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አገናኘው ማሙዬ ለአብመድ እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ውሳኔ የሠራተኞችን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበና ተገቢነት የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም ቀጣይ መስተካከል በሚችልበት መልኩ ውይይት ማድረግ እንደሚገባም ነው ምክትል ኃላፊው የገለጹት፡፡
ለቅሬታ አቅራቢዎቹ ሥራው እንደ ‹አውት ሶርስ› ተደርጎ በተናጠል ደመወዝ እንደተሰጣቸውና ወርኃዊ ደመወዛቸውም 941 እና 1586 ብር እንደሆነ አመልክተው በዚህ ወጣቶቹ አትራፊ ስላልሆኑ ሽግግሩ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ይኼነው አስረድተዋል፡፡ ‹‹የተደራጁት ወጣቶች በጨረታ ቢገቡ ኖሮ በአነስተኛ የሰው ኃይል በመሥራት አትራፊ መሆን ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን ለምሳሌ የጽዳት ሠራተኞች መጀመሪያ 30 ነበሩ አሁን ግን ተጨማሪ ሰው ተቀጥሮ 90 ደርሰዋል፤ በኮንትራት ወስደውት ቢሆን ኖሮ ግን በጥቂት ሰው ሥራውን በመሸፈን አትራፊ ይሆኑ ነበር›› ሲሉም ሽግግር ማድረጉ አሳማኝ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

Previous article“ፍትሕ ያጣ ሕዝብ ፍትሕን በእጁ ይፈልጋል፤ ይህ እንዳይሆን ደግሞ መንግሥት ወንጀል የሚሠሩ አካላትን ወደሕግ ማቅረብ አለበት፡፡” ምሁራን
Next articleየስዊድን የጤና እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር የሚመራ ልዑካን ቡድን ጤና ሚኒስቴርን ጎበኘ፡፡