በሰሜን ሸዋ ዞን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የተበጀተላቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መኾኑን የዞኑ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

86
ደብረ ብርሃን :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመምሪያው ኀላፊ ችሮታው አስፋው ለአሚኮ እንደተናገሩት የመስኖ ፕሮጀክቶቹ እስከ ሁለት ዓመት በሚወስድ ጊዜ ተገንብተው ይጠናቀቃሉ ብለዋል።
በዞኑ ሞጃና ወደራ ወረዳ አይሶፌ ቀበሌ በ280 ሚሊዮን ብር የመስኖ ካናል ለመገንባት ሥራ ተጀምሯል።
የመስኖ ካናሉ ከ400 በላይ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲኾን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል።
በክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ በጀት የሚገነባው የመስኖ ፕሮጀክቱ ጢስ እሳት ኮንስትራክሽን ግንባታውን ያከናውናል። ይህ ፕሮጀክት በ24 ወራት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አሚኮ ያናገራቸው አርሶ አደሮች ካሁን በፊት በዘልማድ አሰራር በመስኖ ሲጠቀሙ እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ላይ ይህ ካናል ሲገነባ ደግሞ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ነው የተናገሩት።
በሰሜን ሸዋ ዞን እምቅ የመስኖ አቅም እንዳለ ያነሱት አቶ ችሮታው በኩላቸው ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር መልማት የሚችል ሁሉም መሬት እንዲለማ እየተሠራ ስለመኾኑ አስረድተዋል። በዞኑም ትንንሽ የመስኖ ካናሎችን ሳይጨምር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ኤልያስ ፈጠነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቀረበበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ በፍፁም አይቀበልም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።