“የለውጥ አመራሩ ያለፍንበትን ሀገራዊ ሂደት ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፋዊውን የጎራ ልዩነትም መረዳት አለበት” ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ

140
ባሕር ዳር :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ድሎችን የማጽናት እና ፈተናዎችን የመሻገር ወቅታዊ እና ታሪካዊ ያለውን የአመራር ውይይት በባሕር ዳር ዛሬ ጀምሯል፡፡ በውይይቱ ከፌደራል እስከ ወረዳ ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ይሳተፋሉ፡፡ ውይይቱ በወቅታዊ ሀገራዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ተነጋግሮ የጋራ ተልዕኮ ለመያዝ ያለመ ነውም ተብሏል፡፡
ውይይቱን የከፈቱት የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ የለውጡ ጉዞ በርካታ ፈታናዎች እና የበዙ መልካም ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር ብለዋል፡፡ ፈተናዎችን እያለፉ መልካም ዕድሎችን መጠቀም የበሰለ መንገድ ነው ያሉት ዳይሬክተር ጀኔራሉ በበርካታ ውጣ ውረዶች የታጀበው ያለፉት አራት ዓመታት ሀገራዊ ጉዟችን ሁሉንም በሚዛን ያስተናገደ ነበር ነው ያሉት፡፡
ዓለም አቀፋዊ ኹኔታው ለአፍሪካ ሀገራት ፈተና የኾነበት ወቅት ላይ ነን ያሉት አቶ ተመስገን “የምሥራቁ እና የምዕራቡ” የሚል ጎራ ለይተው የሚፋለሙ ሀገራት ለበርካታ ድሀ ሀገራትም ፈተና ኾነዋል ብለዋል፡፡
እንደ አህጉር በአፍሪካ፣ እንደ ሀገርም በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ጎራ ለይተው የሚፋለሙት ሃያላን ፤ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖዎችን እንደሚያሳርፉባቸው መረዳት ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡
“የለውጥ አመራሩ ያለፍንበትን ሀገራዊ ሂደት ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፋዊውን የጎራ ልዩነትም መረዳት አለበት” ነው ያሉት፡፡
ውይይታችን የገጠሙንን ሀገራዊ ችግሮች በምናይበት ልክ፤ ያስመዘገብናቸውን ድሎች መዘንጋትም የለበትም ያሉት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ የውይይታችን ማዕቀፍ ከገጠሙን ፈተናዎች፣ ካስመዘገብናቸው ድሎች፣ ከተለምናቸው የልማት ፕሮጀክቶች እና ከምንደርስባቸው ታላላቅ ራዕዮች የሚመነጭ መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡
ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን እንዳሉት እንደ ሀገር ተገዳዳሪዎቻችን ከህጸጾቻችን መድከማችንን፤ ከፈተናዎቻችን መውደቃችንን የሚመኙ መኾናቸውን አንስተው ውስጣዊ ልዩነታችንም ከዚህ የተሻለ አሰላለፍ የለውም ነው ያሉት፡፡ በመኾኑም በየደረጃው የሚገኘው አመራር ችግሮችን ማቀንቀን ብቻ ሳይኾን መፍትሄ አመላካች የኾነ ግልጽ ውይይት ማድረግም ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ውይይታችን ለገጠሙን ጥቃቅን ችግሮች መፍትሄዎችን እያበጀ የሚያሻግር ይኾናል ብየ አስባለሁ ያሉት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ሀገራዊ ራዕያችን እና ታላላቅ ትልሞቻችን የውይይታችን ማዕቀፍ ይኾናሉ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበ90 ቀናት ከ3000 በላይ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት ማስጀመር የሚያስችል የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈረመ፡፡
Next article“የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቀረበበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ በፍፁም አይቀበልም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር