በ90 ቀናት ከ3000 በላይ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት ማስጀመር የሚያስችል የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈረመ፡፡

57
ባሕር ዳር :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር አሥተዳደር ዞን የ17 ወረዳ አሥተዳዳሪዎችና ከንቲባዎችበቀጣይ 90 ቀናት 3 ሺህ 200 መማሪያ ክፍሎችንና የጤና ፕሮጀክቶችን አጠናቀው ለተጠቃሚ ማስረክብ የሚያስችል የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመዋል ፡፡
አማራ ልማት ማኅበር ከማዕከላዊ ጎንደር ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር “ኑ ! ትውልድ እንገንባ ! ” በሚል መሪ መልዕክት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ የምክክር መድረክ በዞኑ የሚገኙ 1019 አንደኛ ደረጃና 51 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመገኘታችው ምክንያት ባለፉት ሶስት ዓመትት ብቻ የተማሪዎች ውጤት እጅግ እያሽቆለቆለ መምጣቱን በሰፊው ከተወያዩና ደረጃቸውን ለማሻሻል ከተስማሙ በኋላ ነው፡፡
የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ መላኩ ፈንታ እና የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ክቡር አቶ ወርቁ ሀይለማሪያምን ጨምሮ የሁሉም ወረዳ አሥተዳዳሪዎች፣ ከንቲባዎችና የትምህርት አመራሮች በተሳተፉበት መድረክ ዞኑ በትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ በቀጣይ 90 ቀናት ኅብረተሰቡን በማስተባበር የዞኑን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃ የሚያሻሽሉ 3ሺህ 200 የመማሪያ ክፍሎችን ገንብተው ለአገልግሎት ዝግጅ ማድረግ የሚያስችል መተማመንና መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ትውልድ ባንድ ቀን ባይገነባም ዛሬ መሰረት መጣል ይቻላል ! የሚል የጋራ አቋም የወሰዱት የማዕከላዊ ዞን ሁሉም ወረዳ አመራሮችና ከንቲባዎች ለችግሩ በርካታ ምክንያት መደርደር ቢቻልም በወረዳና በከተማ አሥተዳደር አቅም ሊፈታ እየተገባ እስካሁን በቅንጅት ባለመሰራቱ ለትምህርት ሥርዓቱ መጓደል የችግሩ ዋና ምክንያት ተደርጎ ተለይቷል፡፡
በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የተጓደሉትን የንፁህ መጠጥ ውሀና የመፀዳጃ ቤት ግንባታ፣ የስፖርት ማዘውተሪያና ትምህርት ቤቶችን የማስዋብ ተግባር በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክት ትግበራ ዋነኛ የንቅናቄ ማዕከል አድርጎ በመስራትና ኅብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ችግሩን እስከ ሰኔ ሰላሳ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን የዞኑ አሥተዳዳሪ ክቡር አቶ ወርቁ ሀይለማሪያም አስረድተዋል፡፡
ያጋጠመንን የትምህርት ስብራት በየጊዜውና በየመድረኩ ከማንሳት የሁሉም ኅብረተሰብ የርብርብ ማዕከል ማድረግና በውስጥ አቅም ለመፍታት ዞኑ የወሰደው አቋም ለሌሎች የክልላችን አካባቢዎችም እጅግ ትምህርት ሰጭ መሆኑን የአማራ ልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ መላኩ ፈንታ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው በዞኑ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ተደርጎላቸዋል፡፡ መረጃውን ያገኘነው ከአማራ ልማት ማኅበር ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሎሬት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
Next article“የለውጥ አመራሩ ያለፍንበትን ሀገራዊ ሂደት ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፋዊውን የጎራ ልዩነትም መረዳት አለበት” ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ