
ባሕር ዳር :መጋቢት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በብዝሃ ሕይወት ሳይንቲስትነት አንቱታን ያተረፉት ሎሬት ዶክተር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ባደረባቸው ሕመም በ83 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ እና ተከራካሪ የነበሩት ዶክተር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔር ከአባታቸው ከቄስ ገብረእግዚአብሔር ዮሐንስ እና ከእናታቸው ወይዘሮ መዓዛ ወልደ መድኅን በትግራይ ክልል ዐድዋ ርባገረድ መንደር የካቲት 12 ቀን 1932 ዓ.ም ተወለዱ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ 1ኛ ደረጃ እንዲሁም ወደ ጀኔራል ዊንጌት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማምራት በ1959 ዓ.ም በከፍተኛ ውጤት ወደ ቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል።
ሎሬት ዶክተር ተወልደብርሃን በሕይወት ዘመናቸው ለሀገራቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና አርዓያነታቸው በጉልህ ቀለም ከሚጻፍላቸው ጀግና ኢትዮጵያዊያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡ ነበሩ።
በብዝሃ ሕይወት ጥናት እና ምርምርም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት ችለዋል።
ዶክተር ተወልደ ብርሃን የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ሲሆኑ ከ60 በላይ ሌሎች ልጆችን ያሳደጉ ልበ ቀና ሰው ነበሩ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!