‹‹ዩኒቨርሲቲው እንደ ዓይን ብሌን የምናየው ተቋም ነው::›› በእንጅባራ ዩነቨርሲቲ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶች

235

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2012 ዓ.ም (አብመድ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም ነበር የመማር መስተማር ሥራውን የጀመረው፡፡ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በምርምር እና ማኅበረሰብ አግልግሎት ዘርፍ የእንጅባራን እና የአካበቢውን ማኅበረሰብ ለማገልገል ሰፊ ዕቅድ ነድፎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እስካሁን በአመራር ጥበብ፣ የአካበባቢውን ባሕላዊ ትውፊቶች በማሳደግና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በስፋት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ተቋሙ በአዊ ባሕል፣ በግብርና ዘርፍ እና የአዊኛ ቋንቋን በማበልጸግ ላይ ዕቅድ ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገም ነው፡፡ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በተለያዩ ሥራዎች እንዲሠማሩ በማድረግ ከ700 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡

አቶ አበባው አይነታው በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተቀጥሮ የሚሠራ ወጣት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመቋቋሙ በፊት ምንም ሥራ እንዳልነበረውም ተናሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በእንጅባራ ከተማ መከፈቱን ተከትሎ በ2011 ዓ.ም በከተማ አስተዳድሩ ቴክኒክ ሙያ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት የተደራጁ ወጣቶችን በማስልጠን ወደ ተለያዩ ሥራዎች እንዲገቡ በር ክፍቷል፡፡ አበባው በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ከሚያገኘው ገቢ 15 በመቶ እንደሚቆጥብ ተናግሯል፡፡ “እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ እንደ ዓይን ብሌን የምናየው ተቋም ነው” ያለው አበባው በሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑት ብዙ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

የእንጅባራ ከተማ አስተዳድር ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ቀለሙ እንደ ተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በከተማዋ ላይ መከፈቱ ብዙ የሥራ ዕድል ፀጋዎች እንደፈጠሩ አስችሏል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ እንኳን 114 ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት በጥበቃ፣ በውፍጮ ቤት፣ በጽዳት እና በተማሪዎች አግልግሎት ሥራዎች እንዲሰማሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ለመጪው ጊዜም ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመነጋገር አስፈላጊ የሰው ኃይል እንደሚያቀርቡ መወያየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲው እንጅባራ ከተማ ላይ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርጓል›› ብለዋል፡፡

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለሀገርም ለአካባቢውም ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ቦታቸውን ለዩኒቨርሲቲው የሰጡትን ዜጎች ከ30 እስከ 40 በመቶ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ‹‹የትምህርት ደረጃ የሌላቸውን እና በሙያ በጣም ጥሩ የሚሠሩ እናቶችን በዩኒቨርሲቲው ተቀጥረው በወጥ ሥራ ላይ ለተማሪዎች አግልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል›› ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው አዲስ ተቋም በመሆኑ የሰው ኃይል እና የመሠረተ ልማት በማሟላት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በሚቀጥሉት ዓመታት የምርምር ሥራዎችን በመሥራት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከማገልገል ጎን ለጎን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማደርግ በዕቅድ እየሠራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ 4ሺህ 500 ነባር እና አዲስ ተማሪዎች በመማር ላይ እንደሚገኙ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleበ፩ኛው የአማራና ኪነ ጥበብ ጉባኤ ማጠቃለያ በኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዕውቅና ተሰጣቸው፡፡
Next article“ፍትሕ ያጣ ሕዝብ ፍትሕን በእጁ ይፈልጋል፤ ይህ እንዳይሆን ደግሞ መንግሥት ወንጀል የሚሠሩ አካላትን ወደሕግ ማቅረብ አለበት፡፡” ምሁራን