
ጎንደር :መጋቢት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ”ኑ ትውልድ እንገንባ” በሚል መሪ መልዕክት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
እንደ ሃገር የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ትምህርት ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ ከቀበሌዎች ጀምሮ የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ የወረዳ እና የዞን ኀላፊዎች እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ኢየሩስ መንግስቴ በተለያዩ ሃገራት የሚታዩ ችግሮች ዋና ማጠንጠኛ ችግራቸው የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነት የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በ2012 ዓ.ም ወስደው የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 49 ከመቶ መሆናቸውን አስታውሰው በ2013 ወደ 14 ከመቶ ዝቅ ሲል በ2014 ደግሞ ወደ ሶስት ከመቶ ዝቅ ማለቱ የትምህርት ሥርዓቱ የገጠመውን ችግር ማሳያ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ሃገራችን ካለችበት ችግር መውጣት ከተፈለገ የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻል አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በየደረጃው ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
ሁሉም መስራት በሚገባው ልክ ባለመስራቱ እንደ ሃገር አሁን ያለው ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሃይለማርያም ናቸው።
የምክክር መድረኩ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የገጠሙ ችግሮች ላይ ለመወያየትና ለማስተካከል ያለመ መሆኑንም አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!