“አዲሱ ድልድይ የከተማዋን ቱሪዝም የሚያሳድግ እና የትራንስፖርት ፍሰትን የሚያሻሽል ነው” የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)

64
ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ትልቁና ረጅም ጊዜ የወሰደው አዲሱ የዓባይ ድልድይ የመገጣጠሚያ ሙሌት ሥራ ተጠናቋል።
አዲሱ የባሕርዳር ድልድይ የመገጣጠሚያ ሙሊት ሥራ ተጠናቋል። በሁለቱም አቅጣጫ ሲካሄድ የነበረው አዲሱ የባሕርዳር ድልድይ ወንዙ መካከል ላይ የመገጣጠሚያ ሙሊት የማካሄድ ሥራው ነው ትናንት ምሽት የተጠናቀቀው። የመገጣጠሚያ ሙሊቱን ምክንያት በማድረግም የማብሠሪያ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በማብሰሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ለከተማዋ ታላቅ ብሥራተ እና ድል ነው ብለዋል። የመጨረሻው የመገጣጠሚያ ሙሊት የማጠናቀቂያ ሥነ ሥርዓት መካሄዱንም ገልፀዋል።
አዲሱ ድልድይ የከተማዋን ቱሪዝም የሚያሳድግ እና ትራንስፖርት ፍሰትን የሚያሻሽል ነው እንደሆነም አስረድተዋል። ታላቁ ሥራ ተጠናቋል ያሉት ዶክተር ድረስ ቀጣይ የሚቀሩ ሥራዎች በቀጣይ ጊዜያት ይከናወናሉ ብለዋል።
ፕሮጄክቱ እስከ ሰኔ 30 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልፀዋል። በከተማ አስተዳደሩ በኩል የሚጠበቁ ሁሉንም ሥራዎች ቀደም ብለው ማጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል። ተቋራጩን የማበረታታት እና የግብዓት አቅርቦት ችግር ሲገጥም መፍትሔ የመሥጠት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የአዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ምክትል ተጠሪ መሐንዲስ ፍቅረሥላሴ ወርቁ ረጅም ጊዜ የወሰደውና የፕሮጄክቱ ትልቁ ሥራ ተጠናቋል ነው ያሉት። በቀኝ እና በግራ ሢሠራ የነበረው የመጨረሻ የመገጣጠሚያ ሙሊት ማለቁንም ገልፀዋል። ይህም የድልድዩን 3 መቶ 80 ሜትር መጠናቀቂያ የሚያበስር ነውም ብለዋል። ፕሮጄክቱ 94 ነጥብ 15 በመቶ መጠናቀቁንም ገልፀዋል።
May be an image of 6 people and text that says 'ANA ኦን ኦንላይን ሚደያ'
ሰኔ 30 ላይ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየሠራን ነውም ብለዋል። አዲሱ የዓባይ ድልድይ 3 መቶ 80 ሜትር ርዝመት በ43 ሜትር ሥፋት የሆነ ታላቅ ድልድይ መሆኑንም ገልፀዋል።
አዲሱ የባሕዳር ድልድይ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ውበት በመጨመር፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን በማፋጠን እና የቱሪዝም ፍሰቱን ከፍ በማድረግ ለከተማዋ ታላቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleራያ እና ወልቃይት የመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ድምቀት ኾነው ውለዋል።
Next article“በወጪ ንግድ ሥርዓቱ ክፍተት ከሀገሪቱ የተለያዩ ምርቶች በሕገ ወጥ መንገድ ይወጣሉ” አቶ ደመቀ መኮንን