
ባሕር ዳር:መጋቢት 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የሶውል ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ አሸነፈ።
የሴዑል ማራቶን ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩ ውድድሮች አንዱ ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1931 የተጀመረ ነው።
ትናንት ምሽት 77ኛው የሶውል ማራቶን ውድድር ተካሂዷል።
በውድድሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።
በ2014ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በተካሄደው የኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን ውድድርና በ2013ዓ.ም በህንድ ኤርቴል ግማሽ ማራቶን አሸናፊ የነበረው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ የሶውል ማራቶንን አሸንፏል።
አትሌት አምደወርቅ ውድድሩን ለመጨረስ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ ወስዶበታል።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሽፈራ ታምሩ ደግሞ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ38 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ጨርሷል።
አትሌት ሃፍቱ አሰፋ ደግሞ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው 76ኛው የሶውል የወንዶች ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!