
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 23/2012 ዓ.ም (አብመድ) የጎንደርን ታሪክ የሰነደ 339 ገጽ ያለው የታሪክ መጽሐፍ ‹‹የመማጸኛ ከተማ- (የ44 ሀገር)›› በሚል ርዕስ ዛሬ ጎንደር ላይ እየተመረቀ ነው፡፡
በጎንደር የሥልጣኔ ዘመን የተሠሩ ልዩ ልዩ ታሪኮችንና የታሪክ አጋጣሚዎችንና የጎንደር ቀለማት የሚባሉትን 44 ታቦታትን ስያሜዎች በተናጠል እስከ ታሪካቸው ያካተተ መጽሐፍ ነው እየተመረቀ ያለው፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ጎንደር ለሀገር ሠላም ተማጻኝ፣ የሃይማኖት ሀገርና የሠላም ተምሳሌት መሆኗንና የመማጸኛ ከተማነቷን በአስረጅነት የያዙ ታሪኮች ቀርበዋል፡፡
በጎንደር ታሪክ ዙሪያ የታሪክ አዋቂዎች ተጠይቀውና የታሪክ ሰነዶች ተፈትሸው በጥናት ተደግፎ የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑ ለአንባቢውና ለቀጣይ ትውልድ ትክክለኛ ታሪክን ለማሸጋገር እንደሚጠቅም ተገልጿል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡ በታምራት ወርቁ የተዘጋጀው መጽሐፉ በ150 ብር ለአንባብያን የቀረበ ነው፡፡
በጎንደር ከተማ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና የሃይማኖት አባቶች ከጥቅምት 07 ቀን ጀምሮ ስለኢትዮጵያ ሠላምና አንድነት ጸሎተ ምሕላ ላይ ናቸው፤ የማኅበረ ሥላሴ ገዳም የሃይማኖት አባቶችም ከነገ ጀምሮ ጸሎተ ምሕላ አዝዘዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ዑለማ እና የከተማ አስተዳደሩ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትም በየአምስት ወቅት ሶላት የቅኑስ ዱዓ በየመስጂዱ ጀምረዋል፤ ዱዓው ለአንድ ወር የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል፡፡ የቅኑስ ዱዓ ሀገር አጣብቂኝ እና ፈታኝ ሁኔታ ላይ ስትሆን የሚደረግ ዱዓ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- እመቤት ሁነኛው -ከጎንደር