
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 23/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል በ2011/12 የምርት ዘመን ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሊፈጠሩ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ‹‹የተቀናጀ አሠራር፣ ተከታታይ ቅኝት እና አሰሳ ማድረግ ያስፈልጋል›› ተብሏል፡፡
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዘንድሮው ድርቅ በስፋት ከተከሰተባቸው አካባቢዎች መካከል የሳህላ ሰየምት እና ዝቋላ ወረዳዎች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ድርቁ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና የምግብ ችግር የሚያስከትል በመሆኑ ከሥነ ምግብ እና ንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የጤና ችግሮች ይኖራሉ ነው የተባለው፡፡ ሊፈጠሩ የሚችሉ የጤና ችግሮች በሰው ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የወረርሽኝ ምላሽ ኮሚቴ ማቋቋም እና የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የስሃላ ሰየምት ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የዕቅድ ዝግጅት እና የሕጻናት ጤና ባለሙያ አቶ ጌትነት መርሻ በተለይም ለአብመድ በሰጡት አስተያየየት ‹‹ወረዳው ድርቁን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ ርሃብ፣ የወባ፣ ኮሌራ እና ሌሎች የወረርሽኝ በሽታዎችን የሚከታተል የወረርሽኝ ምላሽ ኮሚቴ ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በተውጣጣ መልኩ ተቋቁሟል›› ብለዋል፡፡
የተቋቋመው ኮሚቴ እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ እና ነባራዊ ሁኔታውን በመመልከት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እና ዕቅድ አዘጋጅቶ ከመንግሥትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ጥረት እያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
‹‹በወረዳው ውስጥ በተደረገ ዳሰሳ በሕጻናት፣ ነፍሰ ጡር እና አጥቢ እናቶች ላይ የምግብ እጥረት ችግር እንዳለ ያሳያል›› ያሉት ባለሙያው በወረዳው ውስጥ ለሚገኙ የዕርዳታ ድርጅቶች የሕጻናት አልሚ ምግብ፣ የውኃ ማከሚያ እና የመድኃኒት አቅርቦት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የሕጻናት አልሚ ምግብ እደላ በወረዳው ውስጥ በሚገኙ ሦስት ጤና ጣቢያዎች እና 13 ጤና ኬላዎች ላይ መጀመሩንም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይህ ግን ያለውን የምግብ እጥረት ሙሉ በሙሉ ይፈታል ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም ለአንድ ሕጻን የተሰጠ አልሚ ምግብ በቤት ውስጥ ላሉ ሌሎች ልጆች የማከፋፈል ልማድ ይስተዋላልና›› ነው ያሉት ባለሙያው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የዝቋላ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ማሞ እንደገለፁት በወረዳው ውስጥ ባሉ ቀበሌዎች በተደረገ ዳሰሳ ከ800 በላይ የሚደርሱ ሰዎች ከድርቁ ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችሉ የጤና ችግሮች ተጋላጭ የሚያደርጉ ምልክቶች ታይተውባቸዋል፡፡ ችግሩን ለመከላከል ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠሩ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው የወረዳው አስተዳደር ምክር ቤት 250 ሺህ ብር እና ምግብ ለተራቡ ዓለማቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያ (ኤፍ ኤች አይ) 260 ሺህ ብር በመመደብ አልሚ ምግብና መድኃኒት መገዛቱን እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
በውኃ እጥረት ምክንያት ሰው እና እንስሳት በአንድ ላይ ለመጠጣት ስለሚገደዱ የአባ ሰንጋ በሽታ (አንትራክስ) ሊከሰት ይችላል ተብሎ እንደሚሰጋም ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከድርቁ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሰው እና የእንስሳት የጤና ችግሮችን ለመከላከል የተቀናጀ ሥራ እና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አቶ ደሳለኝ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው -ከዝቋላ